Search

የመደመር ትውልድ፡- በትናንትና እና በነገ መካከል የቆመ የልማትና የእድገት ድልድይ

ሰኞ መስከረም 18, 2019 127

ትውልድ የጊዜ ሂደት ውጤት ብቻ ሳይሆን፣ የኃላፊነትና የታሪክ ውርስ ተሸካሚም ነው። በታሪክ አጋጣሚ "የመደመር ትውልድ" ተብሎ የሚጠራው የዘመናችን ትውልድ፣ በትናንትና እና በነገ መካከል ባለው ወሳኝ መስቀለኛ መንገድ ላይ ይገኛል።

ትናንት ያለፈና የተጠናቀቀ የታሪክ ምዕራፍ ሲሆን፣ ነገ ደግሞ ገና ያልተጻፈ ነገር ግን በዛሬው ብዕራችን የምንቀርጸው ተስፋችን ነው።

በእነዚህ ሁለት ዘመናት መካከል የቆመው የዛሬው ትውልድ ታላቅ የታሪክ ውል አለበት፤ ትናንትን በዛሬ ሥራው ክብር ማልበስ፣ ነገን ደግሞ በዛሬ ትጋቱ አሳምሮ መገንባት።

ትናንት ለአንድ ሕዝብ የመሠረት ያህል ነው። ያለ ትናንት ታሪክ፣ ባህልና መሥዋዕትነት የዛሬ ማንነታችን ሊታሰብ አይችልም።

አባቶቻችንና እናቶቻችን ለዚህች ሀገር ነፃነት፣ ሕልውናና ባህላዊ እሴት ሲሉ የከፈሉት ዋጋ ቀላል አልነበረም። ነገር ግን የታሪክን ክብር ማቆየት የሚቻለው ስለ ትናንት ድልና ጀግንነት በመፎከርና በማወደስ ብቻ አይደለም።

ትናንትን በእውነት ክብር ማልበስ የሚቻለው አባቶቻችን የተውልንን አዎንታዊ እሴቶች በመጠበቅ፣ የሠሩትን መልካም ነገር አጠናክሮ በማስቀጠልና የተሳሳቱትን ደግሞ በዛሬው ብልህነታችን በማረም ነው።

የትናንት መሥዋዕትነት ዋጋ የሚያገኘው ዛሬ ላይ ተቀምጠን በነበሩ ችግሮች ላይ ስንማረር ሳይሆን፣ የትናንቱን ታሪክ መነሻ አድርገን ለዛሬው ችግራችን መፍትሔ ስናመጣ ነው።

በዛሬው ውጤታማ ሥራችን፣ በሰላማችንና በልማታችን የትናንቶቹን ውድ ዋጋ ትርጉም እንሰጠዋለን።

በሌላ በኩል፣ የነገዋ ኢትዮጵያ በዘፈቀደ የምትፈጠር አይደለችም። የነገዋ ሀገር ዛሬ በምናስቀምጠው መሠረት፣ በምንዘራው የመልካምነት ዘርና በምናፈሰው ላብ የምትወሰን ናት።

የመደመር ትውልድ የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ ብቻ የሚጠብቅ ሳይሆን፣ ተስፋውን በእጁ ሥራ ወደ እውነታ የሚቀይር ትውልድ ነው።

ነገ አምራች፣ የበለጸገች፣ የተረጋጋችና ለዜጎቿ የምትመች ሀገር እንድትሆን ከተፈለገ የዛሬው ትጋት ወሳኝ ነው። ትጋት ሲባል በየተሰማራንበት ሙያ በግብርናው፣ በቴክኖሎጂው፣ በትምህርቱ፣ በንግዱና በሥራ ፈጠራው ጥራት ያለውና ዘላቂ ውጤት የሚያመጣ ሥራ መሥራት ማለት ነው።

ዛሬ የምናሳየው የሥራ ባህል፣ የምንገነባው ተቋማዊ አቅምና የምንተክለው የአንድነት እሴት ለነገው ትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ ሀብት ነው።

የመደመር እሳቤ መሠረቱ የነበረውን በጎ ነገር አቀናጅቶ መያዝ እና ለተሻለ ነገ ተጨማሪ አቅም መፍጠር ነው።

በመሆኑም የመደመር ትውልድ የታሪክ ተመልካች ሳይሆን የታሪክ ሰሪነት ሚናውን መረዳት አለበት። ትናንትን በሥራችን እያከበርን፣ ነገን በትጋታችን እያሰመርን ስንራመድ ኢትዮጵያ ከነበረችበት የከበረ ታሪክ ወደምትመጥነው ታላቅ የብልጽግና ማዕረግ ትሸጋገራለች።

የዛሬዋ እያንዳንዷ ደቂቃና እያንዳንዷ ጥረት የዚሁ ታላቅ ህልም መሠረቶች ናቸው።

 

በአድማሱ አራጋው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: