Search

ኢትዮጵያ ከቀይ ባሕር ተገልላ የምትኖርበት ሁኔታ መክተም አለበት"፡- ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ

ሰኞ መስከረም 18, 2019 120

ኢትዮጵያ ከታሪካዊ የባሕር በር እርስቷ ተገልላ የምትኖርበት ሁኔታ ማብቃት እንዳለበትና የባሕር በር ማግኘት የነገን ደኅንነት የማስጠበቅ አጣዳፊ የሕልውና ጥያቄ መሆኑን የውኃ ሳይንስ ተመራማሪ ፕሮፌሰር አድማሱ ገበየሁ ገለጹ።

ፕሮፌሰር አድማሱ ከኢቢሲ ጋር ባደረጉት ቆይታ ቀደምት የኢትዮጵያ ወሰን ቀይ ባሕር እንደነበር አስታውሰው፣ ሀገራችን በታሪክ አጋጣሚዎች የባሕር በሯን ማጣቷ በትውልዱ ትልቅ ቁጭትና ክፍተት መፍጠሩን ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ ስትራቴጂያዊ የውሃ መንገድ በሆነው በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ-ሰላጤ አካባቢ የሚስተዋለው የጂኦ-ፖለቲካ ውጥረት፣ የባሕር ወንበዴዎች እንቅስቃሴና የሁቲዎች ጥቃት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ብሔራዊ ደኅንነት ላይ ስጋት እንደደቀነ አንስተዋል።

ቀጣናው ከዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ 12 በመቶ የሚከናወንበት በመሆኑ፤ የቀይ ባሕር መስመር ከተስተጓጎለ መርከቦች አፍሪካን  ዙረው ለመጓዝ ተጨማሪ ከ10 ቀን እስከ ሁለት ሳምንታት ስለሚወስድባቸው ከፍተኛ የኢኮኖሚና የትራንስፖርት ጫና እንደሚያሳድር ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የራሷን ሚስጥራዊና ብሔራዊ ጉዳዮችን በተከራየችው ወደብ ሙሉ በሙሉ ማስከበር አትችልም ያሉት ፕሮፌሰር አድማሱ፣ የቅርብም ሆኑ የሩቅ ሀገራት በሚፈጥሩት ተጽእኖ የኢትዮጵያ እጣ ፈንታ ሲፈተን መኖር የለበትም፤ ኢትዮጵያ በራሷ የምታዝበትና የምትቆጣጠረው የባሕር በር ያስፈልጋታል ብለዋል።

በሌላ በኩል ወጣቱ መርከበኛ መሐመድ ጨክን በሰጠው አስተያየት፤ በሥራ አጋጣሚ ወደተለያዩ የዓለም ወደቦች በሚጓዝበት ወቅት የኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆን ከፍተኛ ቁጭት እንደሚፈጥርበት ገልጾ፣ ይህ ታሪካዊ ስህተትና እውነታ ሊቀየር እንደሚገባ ተናግሯል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከዚህ ቀደም ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በቀይ ባሕር ላይ የማይናወጥ ብሔራዊ ጥቅም እንዳላት ገልጸው፣ "የቀይ ባሕር ባለቤትነት በሰላማዊ መንገድና በህጋዊ አሠራር ለኢትዮጵያ ያስፈልጋታል፤ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ይዞ ያለ ባሕር በር ተቆልፎ መኖር ተገቢ አይደለም፤ ነገር ግን ፍላጎታችንን በጦርነትና በኃይል ማሳካት አንፈልገውም" ማለታቸው ይታወሳል።

አካባቢው ዘላቂ ሰላም እንዲኖረውና የንግድ ልውውጡ በሰላም እንዲቀጥል የቀጣናው ግዙፍ ሀገር የሆነችው ኢትዮጵያ በባሕር በሩ አጠቃቀምና አስተዳደር ላይ በፍትኃዊነትና በሥርዓት መሳተፍ አለባት።

ኢትዮጵያ በቀጣናው ካሉ ሀገራት የተሻለ የመከላከልና የጸጥታ አቅም ያላት በመሆኑ፤ ይህ አቅሟ በሥርዓት ጥቅም ላይ ቢውል የራሷን ጥቅም ከማስከበር ባለፈ የጎረቤት ሀገራትንም ሰላምና ጥቅም ለማስጠበቅ እንደሚያስችል ፕሮፌሰር አድማሱ ተናግረዋል።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ የባሕር በር ጥያቄ ለወደፊት በሚል የሚተላለፍ የሩቅ ጊዜ አጀንዳ ሳይሆን፤ የትናንት ስህተቶችን በማረም የነገን ብሔራዊ ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚደረግ አጣዳፊ ጥያቄ መሆኑ ተገልጿል።

 

በመሐመድ  ፊጣሞ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: