የኢትዮጵያ የልማት ጉዞ ሀገራችንን ከድህነት አዙሪት ለማላቀቅና የኢኮኖሚ ከፍታን ለማረጋገጥ በግንባታ፣ በቴክኖሎጂ እና በግብርና መስኮች በተከናወኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የተረጋገጠ የእድገትና የብልፅግና ተምሳሌት እየሆነ ይገኛል።
ከለውጡ ዓመታት ወዲህ በ"መደመር" እሳቤ በተተገበሩ ስልታዊ የአስተዳደር፣ የፋይናንስ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ሥራዎች ሀገራችን ዘመኑን የሚመጥን አቅም መገንባት ችላለች።
ለዚህ ሀገራዊ ማንሰራራት እና የማድረግ አቅም ማሳያ ደግሞ የአፍሪካ መዲና የሆነችው አዲስ አበባ የፊት መስታወት በመሆን የልማቱ መሪ ምሳሌ ሆና ወጥታለች።
ከተማዋ የአፍሪካ ኅብረት እና የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና መስሪያ ቤቶችን ጨምሮ የበርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት እና ኤምባሲዎች ማዕከል ናት።
በዚህም በቅርብ ዓመታት ያከናወነቻቸው ሰፊ የመልሶ ማልማት፣ የኮሪደር ልማት፣ የፓርኮች ግንባታ እና የመሰረተ ልማት ማሻሻያዎች ገፅታዋን ሙሉ በሙሉ በመቀየር የኢትዮጵያን ሁለገብ የማንሰራራት አቅም በተግባር አሳይተዋል።
ይህ የልማት ስኬት ቁሳዊ ግንባታን ብቻ ሳይሆን ሰው ተኮር አቀራረብንም ያቀናጀ ነው። የከተማ አስተዳደሩ በዝቅተኛ የኑሮ የሚገኙ ዜጎችን ቤቶች በማደስ፣ የተቸገሩ ዜጎችን በመደገፍ እንዲሁም አረጋውያን እና ህፃናትን ያማከሉ የበጎ አድራጎት ስራዎችን በማከናወን አቃፊ ልማትን በአርዓያነት አስመስክሯል።
እነዚህ ሥራዎች ከተማዋ የምሥራቅ አፍሪካ የንግድ፣ የኢንቨስትመንት እና የቱሪዝም መዳረሻ እንድትሆን ከማስቻላቸው ባሻገር፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎትና በግል ሥራ ፈጠራ ለብዙ ወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጥረዋል።
ታሪካዊ ቅርሶቿን ከዘመናዊ የከተማ ገፅታ ጋር ያቀናጀችው አዲስ አበባ፣ የፈጠራ እና የባህል ማዕከል በመሆን ብዝሃነትና አብሮነት የሚጎላባት "ትንሿ ኢትዮጵያ"ነቷን አረጋግጣለች።
በአዲሷ አዲስ አበባ እየታየ ያለው ፈጣን እድገትና መዋቅራዊ ለውጥ፣ የታቀዱ ግዙፍ የልማት እቅዶችን በአስተማማኝ ሁኔታና በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ እውን የማድረግ ሀገራዊ አቅም መገንባቱን የሚያስመሰክርና ለቀጣዩ የኢትዮጵያ የብልፅግና ጉዞ ጠንካራ መሰረት ነው።
በብሌን ደምበሎ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: