የሸካቾ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ማሽቃሮ ባሮ” በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል በቴፒ ከተማ በተለያዩ ባህላዊና ልዩ ሁነቶች በታላቅ ድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል።
በክብረ በዓሉ መረሃ ግብር ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የቴፒ ከተማ ከንቲባ አቶ ጌላቲያስ ሻሜ፣ ለዘመናት ተቋርጦ የነበረው የሸካ ባህላዊ አስተዳደር ሥርዓት ተመልሶ በዓሉ በተለየ ድምቀት በሚከበርበት ታሪካዊ ወቅት ላይ መገኘት ትልቅ ኩራት ነው ብለዋል።
በዓሉ የአንድነትና የመቻቻል መገለጫ መሆኑን ያነሱት ከንቲባው፤ ይህንን ድንቅ ባህላዊ እሴት ይዘቱን ጠብቆ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ለማሸጋገር በትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በሌላ በኩል የሸካ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አበበ ማሞ፤ የዘንድሮው “ማሽቃሮ ባሮ” በዓል ሀገራችን ነፃ፣ ፍትሃዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አካሂዳ፣ አዲስ የመንግስት ምስረታ ለማከናወን በዝግጅት ላይ ባለችበት ወሳኝ ወቅት መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ማንነቶች በጋራ የሚኖሩባት ህብረ-ብሔራዊ ሀገር መሆኗን ያነሱት ዋና አስተዳዳሪው፤ የሸካቾ ብሔረሰብ ከጥንት ጀምሮ የራሱ የሆነ የዳበረ ባህላዊ የአስተዳደር ሥርዓት ያለው ህዝብ መሆኑን አብራርተዋል። አክለውም በዓሉ አሮጌው ዘመን አልፎ አዲሱ የሚበሰርበት፣ የክረምቱ ወቅት ተጠናቆ በአብሮነት፣ በፍቅርና በአዲስ ተስፋ የሚከበር ታላቅ በዓል መሆኑን ጠቁመዋል።
በበዓሉ አከባበር ላይ የብሔረሰቡን ትውፊት የሚያንፀባርቁ እና አዲስ ስኬት ሲመዘገብ የሚቀነቀነው “ዩቦ” የተሰኘው ባህላዊ ውዝዋዜ፣ የፈረስ ጉግስ ትርኢቶች እንዲሁም “የጎ” የተሰኘው ባህላዊ የግጥም መድብል ቀርበው የበዓሉን ድምቀት አሳድገውታል።
በዚህ ታላቅ መርሃ ግብር ላይ የሸካቾ ንጉስ ተች ቀጆ፣ የክልል፣ የዞንና የከተማ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ የካውንስል አባላት (ምክራቾዎች)፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የብሔረሰቡ ተወላጆችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የአንድነት፣ የመተሳሰብና የመረዳዳት መገለጫ የሆነው የሸካቾ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል "ማሽቃሮ ባሮ" በሸካ ዞን አንድራቻ ወረዳ ጌጫ ከተማ በነገው ዕለት በከፍተኛ ድምቀት እንደሚከበር ተመላክቷል።
በሰለሞን ንጉሱ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: