Search

ታላቅ ሀገር፣ ታላቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ራዕይ፦ ብሔራዊ ጥቅሟን በራሷ የምታስከብር ሀገር

ማክሰኞ መስከረም 19, 2019 134

ኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዓመታት የታሪካዊ ሥርዓተ መንግሥት፣ የጸና የመንግሥትነት ባህል እና የጽኑ ሉዓላዊነት ባለቤት ናት።

ሀገራችን በየዘመናቱ የሚደቀኑባትን ውስብስብ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ፈተናዎች ተሻግራ በቀጣናው እና በአህጉሩ ገዢ ሚናዋን አስከብራ የዘለቀችው፣ ሕዝቧ በብሔራዊ ጥቅሙ እና በሀገሩ ሕልውና ዙሪያ ባለው ታሪካዊ ተጋምዶ እና ጽኑ ቁርጠኝነት ነው።

ዛሬም ቢሆን ወደ አዲሱ የመንግሥት ምሥረታ የምናደርገው ጉዞ የሚያጠነጥነው “ታላቅ ሀገር፣ ታላቅ ሕዝብ፣ ታላቅ ራዕይ” በሚለው አጠቃላይ መሪ እሳቤ ላይ ሲሆን፣ ይህ ታሪካዊ መድረክ የመደመር መንግሥት የተገበራቸውን የለውጥ እመርታዎች እና በቀጣይ የታለሙ ታላላቅ ሀገራዊ ግቦችን በሚገባ የሚያንጸባርቅ ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ሀገራችን ኢትዮጵያም ሆነች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በርካታ ያልተጠበቁ ፈተናዎችን፣ የጂኦ-ፖለቲካ ውጥረቶችን እና የኢኮኖሚ ጫናዎችን አስተናግደዋል።

ነገር ግን በመደመር መንግሥት መሪነት ኢትዮጵያ እነዚህን እክሎች ወደ ታላቅ ዕድል የመቀየር አስደናቂ የማሸነፍ ጥበብ አሳይታለች። ለምሳሌ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወቅት ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ውድቀት በደቀነበት ወቅት፣ ኢትዮጵያ የዜጎቿን ሕይወት ከመታደግ ባሻገር የሀገር ውስጥ ምርታማነት ሳይስተጓጎል እንዲቀጥል በማድረግ አሸንፋ ወጥታለች።

በተመሳሳይ መልኩ የውጭ ጫናዎች እና ውስጣዊ እክሎች በበዙበት ወቅት፣ በራስ አቅም የመቆም እሳቤን በመተግበር በስንዴ ምርት ራስን ከመቻል አልፎ ለወጪ ንግድ ማብቃት ተችሏል።

ይህ ስኬት ለነገዋ ኢትዮጵያ ተጨባጭ መሠረት በመጣል ለሕዝቡ የታየ እና የሚዳሰስ ተስፋን አረጋግጧል። በቅርቡ መጠናቀቃቸው የተበሰሩት ታላላቅ ፕሮጀክቶች በተለይም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፍጻሜ አግኝቶ በጉባ ላይ የተሰሙ ብሥራቶች የሀገራችንን የኃይል እና የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ያረጋገጡ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪ አዳዲስ የኮሪደር ልማቶች፣ የከተሞች ማዘመን እና የገጠር ሞዴል መንደሮች ልማት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ወደ ተጨባጭ የሕይወት ለውጥ የሚቀየሩ ተስፋዎች ናቸው።

ይህ አዎንታዊ እንቅስቃሴ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ወደ ተጨባጭ ተግባር መሸጋገሩ እና እዚህም እዚያም የሚታዩ ግጭቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚቀለበሱ መሆናቸው ጋር ተያይዞ ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት መሠረት ጥሏል። ኢትዮጵያውያን በጋራ ታሪክ፣ በጋራ ዕድል እና በብሔራዊ ጥቅም ዙሪያ የተሰባሰቡ በመሆናቸው ኅብረ ብሔራዊ አንድነታቸው ይበልጥ እየጠነከረ የመጣ ሲሆን፣ ይህ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚተርፍ አቅም እየፈጠረ ይገኛል።

በዚህ ሁሉ ሂደት የመደመር መንግሥት ሁለንተናዊ የማድረግ አቅም በከፍተኛ ደረጃ ከፍ ማለቱ በተለያዩ ዘርፎች ተረጋግጧል። ኢትዮጵያ በብሪክስ ኅብረት አባልነቷ፣ የዓለም አቀፍ ንግድ ድርጅት አባልነት ሒደቷ እና በባለብዙ ወገን ዲፕሎማሲው መስክ የስበት ማዕከል በመሆን የውጭ ሀገራት እንደፈለጉ የማይዘውሯት እና ብሔራዊ ጥቅሟን በራሷ የምታስከብር ሀገር ሆናለች።

የሀገሪራችንን ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት የማስጠበቅ አቅም በጽኑ መሠረት ላይ የተገነባ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ተፈጥሯዊ ሀብቶቿን የመጠቀም መብቷንም በማረጋገጥ ላይ ትገኛለች።

በተለይም የባሕር በር ጉዳይ የብሔራዊ ደኅንነታችን እና የሕልውናችን መሠረት በመሆኑ፣ ይህንን ማረጋገጥ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናው እና ለዓለም አቀፍ ንግድ መረጋጋት ትልቅ ትርጉም አለው።

ከዚሁ ጎን ለጎን መንግሥት ለሥርዓተ መንግሥት ማጽናት እና ለተቋማት ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ ግለሰቦች ወይም የፖለቲካ አመራሮች ሲቀያየሩ የማይዋዥቁ፣ በሕግ እና በደረጃ የሚመሩ ጠንካራ አገልጋይ ተቋማት ተገንብተዋል። የሀገራችን ሲቪል ሰርቪስም በተጨባጭ መላዋን ኢትዮጵያ እንዲመስል እና የሙያ ብቃትን መመሪያው ያደረገ እንዲሆን ሰፊ መዋቅራዊ ማሻሻያ ተደርጓል።

በአጠቃላይ፣ ሀገር ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ትገኛለች፤ መንግሥትም የሕዝቡን አደራ ተሸክሞ በሙሉ አቅሙ በመሥራት ላይ ነው። ኢትዮጵያ በሺህ ዓመታት የከበረ ታሪኳ፣ በሕዝቧ የማይበገር ጽናት እና በመደመር መንግሥት ጥበበኛ መሪነት የገባችበትን የድህነት እና የመገለል እስረኝነት ሰብራ ወጥታለች።

የተጀመሩት ታላላቅ ፕሮጀክቶች፣ የተገነቡት ጠንካራ ተቋማት እና እየተረጋገጠ ያለው ሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ሉዓላዊነት ኢትዮጵያን በቀጣናው ኃያል እና የማትደፈር ታላቅ ሀገር ማድረጋቸውን ይቀጥላሉ።

በሰለሞን ገዳ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: