Search

“12ኛ ተጫዋች ለመሆን ተዘጋጅተናል” - የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች

ማክሰኞ መስከረም 19, 2019 185

ባሕር ዳር ከ5 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድንን ጨዋታ ታስተናግዳለች።

የጣናዋ ሙሽራ ባሕር ዳር የዋልያዎቹ የድል ቦታ ነች። ወትሮውንም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በዚያ ሲገኝ ከተማዋ የፌስቲቫል አይነት ስሜት ይኖራታል።

ከዋዜማው ጀምራ ያንን ስሜት አምጥታዋለች። በኮሪደር ልማት ይበልጡኑ ለከተማዋ ውበት ኃይል የሆኑት ዘንባባዎቿ ጭምር ለድጋፍ የተዘጋጁ ይመስላሉ። በእግር ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ የሚተምመው ሕዝብ ስሜቱ ሰንደቅ አላማዊ ነው፤ ኢትዮጵያ እንድታሽንፍ የበኩሉን መወጣት።

ለድጋፍ የተዘጋጁ አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ቀለማት እንዲሁም የብሔራዊ ቡድኑ መለያዎችን የለበሱ ብሎም ለሽያጭ ያዘጋጁ አካላትንም ተመልክተናል። ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች እንደሚሉት “በስታዲየም ተገኝተን እናበረታታለን፣ እንደ 12ኛ ተጫዋች ለቡድናችን ኃይል ለመሆን ዝግጁ ነን” ሲሉ ተናግረዋል።

ዋልያዎቹን በሜዳ ተገኝተን ማበረታታት ልምዳቸው እንደሆነ የሚገልጹት ደጋፊዎች፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ሴኔጋልን እንዲያሸንፍ እስከመጨረሻው ድረስ ድጋፋችንን እንሰጣለን ብለዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በባሕርዳር ስታዲየም ካደረጋቸው 8 የነጥብ ጨዋታዎች የተሸነፈው በአንዱ ብቻ ነው። የአፍሪካ ኃያል ቡድን የሆነውን አይቮሪኮስትን 2 ለ 1 ያሸነፈበት ጨዋታ ከማይዘነጉ የባሕርዳር ስታዲየም ድሎች ውስጥ ነው።

ዛሬ ደግሞ የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድንን ይገጥማሉ። በማለዳውም በሺዎች የሚቆጠሩ ደጋፊዎች የባሕር ዳር ስታዲየም መግቢያ በሮች ላይ ጨዋታውን ለመታደም ተሰልፈዋል።

ሴኔጋልን ለማሸነፍ የዋልያው የሜዳ ላይ ፍልሚያ ዋነኛ ቢሆንም “እኛም በድጋፍ ስታድየሙን ለሴኔጋሎች የማይመች እናደርገዋለን” ሲሉ የባሕር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በሀብታሙ ካሴ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: