ኢትዮጵያ በውጫዊ ትርክቶች እንደምትሳለው በችግሮች ውስጥ የምትዋልል ወይም የህልውና አደጋ ያጠላባት ሀገር አይደለችም።
በተጨባጭ መሬት ላይ ባለው እውነት በታሪክ ፈተናዎች ውስጥ አልፋ በጽኑ መሠረት ላይ የቆመች ብርቱ ሀገረ መንግሥት እየገነባች ያለች ሀገር ናት።
የዛሬው ጉዟችን በየጊዜው በሚፈጠሩ ሁነቶች የሚናወጥ ሳይሆን፣ ታሪካዊ መሠረቶቻችንን ጠብቆ በዘመናዊ ዕውቀት እና ተቋማዊ ቁመና እየጠነከረ የሚሄድ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው።
ጠንካራ ሀገረ መንግሥት የሚገነባው በጊዜያዊ ስሜቶች ሳይሆን በጸኑ ተቋማት እና በመግባባት ላይ በተመሠረተ ዴሞክራሲ ነው።
አሁን በሀገራችን እየተከናወነ ያለው ሀገራዊ የምክክር ሂደት እና የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራ የዚሁ ጽኑ መሠረት ማሳያ ነው።
ዜጎች በነጻነት የሚሳተፉበት፣ ሃሳባቸውን በግልጽ የሚያንጸባርቁበት እና ልዩነቶቻቸውን በሰከነ ውይይት የሚፈቱበት የፖለቲካ ምኅዳር መስፋቱ፣ የጋራ ህልውናችንን በማይናወጥ ዓለት ላይ ያኖረዋል።
የሀገረ መንግሥት ግንባታው ሌላው ወሳኝ ምዕራፍ በመንግሥት እና በሕዝብ መካከል እየተገነባ ያለው አዲስ ማኅበራዊ ውል ነው።
ይህ ውል ዜጎች በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ያላቸውን የባለቤትነት ስሜት ከፍ የሚያደርግ ከመሆኑም ባሻገር፣ በመሠረተ ልማት እና በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ታጅቦ የሕዝብን ተጠቃሚነት በተግባር የሚያረጋግጥ ነው።
ማኅበራዊ ውሉ በጋራ ኃላፊነት ሲጠናከር የሀገር ሰላም እና ብልጽግና ከጥርጣሬ ማዶ ወደ ሚጨበጥ እውነታ ይቀየራል።
የኢትዮጵያዊነት ማኅበራዊ ድምር ውጤት የሆኑት ባህላዊ እሴቶቻችን የዚህ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መንፈሳዊ ጉልበቶች ናቸው። የእንግዳ ተቀባይነት፣ የአብሮ መኖር፣ በደስታ እና በሐዘን የመተሳሰብ እንዲሁም የጋራ አጋርነት ልማዶች ትውልድ ሲቀበላቸው የቆዩ ውድ ሀብቶች ናቸው።
ዘመናዊው ሥርዓት ከእነዚህ ጥንታዊ እና የበለጸጉ ማኅበራዊ እሴቶች ጋር ሲጣመር፣ የዜጎችን ሥነ ልቦናዊ አንድነት በማጠናከር ሀገራዊ ከፍታን በፍጥነት ለማረጋገጥ ያስችላል።
እነዚህ የሞራል እሴቶች የውጭም ሆነ የውስጥ ስጋቶችን በመቋቋም ረገድ የጸኑ መከላከያዎቻችን ናቸው።
ኢትዮጵያ እየገነባች ያለው ሀገረ መንግሥት በጠንካራ ተቋማት፣ በዴሞክራሲያዊ መርሆዎች እና በሕዝባዊ እሴቶች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ የትኛውንም ጊዜያዊ ፈተና ተቋቁሞ ወደፊት የሚገሰግስ ነው።
ሀገራችን በውጭ እና በውስጥ ፈተናዎች ተደናቅፋ ሳትቀር በተጨባጭ የዕለት ተዕለት የልማት ሥራዎቿ እና በታደሰ ማኅበራዊ ውል አዲስ ታሪክ እየጻፈች ትገኛለች።
በጋራ እሴቶቻችን ጸንተን በአዲስ መንፈስ ጉዟችንን ስንቀጥል፣ የኢትዮጵያ ብሩህ ከፍታ ከተስፋነት አልፎ በተግባር ይረጋገጣል።
በሔዋን ጌታቸው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: