የአንድ ሀገር የፖለቲካ ብስለት እና የማኅበራዊ መሰረት ጥንካሬ በዋናነት የሚለካው ልዩነቶችን በሰለጠነ መንገድ አስተናግዶ ወደ ብሔራዊ አቅም መቀየር በሚያስችል ተቋማዊ አሰራር ነው።
በርካታ ባህሎች፣ እምነቶች እና ቋንቋዎች ተሳስረው ያቆሟት ኢትዮጵያ ባለፈችባቸው የታሪክ አጋጣሚዎች እንደሚያሳዩት የማኅበረሰብ ስብጥሮች ለግጭት መንስኤ ሳይሆኑ በውይይት ከተቃኙ ዘላቂ ልማት እና የጸና አንድነትን የሚያጎለብቱ ብሔራዊ ጸጋዎች ናቸው።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እውን ለማድረግ እየሠራችበት ያለው የመግባባት ዴሞክራሲ፣ ልዩነትን ጥንካሬ አድርጎ የተገነባን አንድነት ለማጽናት ትልቅ ራዕይ ሰንቋል።
ይህ ሂደት በፅንሰ-ሀሳብ ደረጃ ብቻ የቀረ ሳይሆን በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን እና መሰል ተቋማዊ መድረኮች አማካኝነት በተግባር እየተፈተነ ይገኛል።
በተለይም ኢትዮጵያውያን በውስጣቸው ያዳበሯቸውን እንደ ሽምግልና ያሉ ነባር የችግር አፈታት እሴቶችን ዘመናዊ ከሆነው የዴሞክራሲ ሥርዓት ጋር በማዋሃድ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት የሚደረገው ጥረት፣ ለቀጣናውም ሆነ ለአህጉር ተስፋ ሰጪ ማሳያ ሊሆን የሚችል መደላድል እየፈጠረ ነው።
በታሪክ ሂደት ውስጥ የብሔር እና የባህል ስብጥሮችን እንደ ስጋት የመመልከት የፖለቲካ ትርክት አልፎ አልፎ ጎልቶ የቆየ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በጋራ የመኖር፣ የመቻቻል እና አስቸጋሪ ፈተናዎችን በአንድነት የመሻገር ረጅም ዘመናት ባህላዊ ትስስር አለው።
የባህል እና የቋንቋ ስብጥር የኅብረተሰቡን ማኅበራዊ መሰረት የሚያበለጽግ እንጂ አብሮነትን የሚያዳክም አይደለም።
ኢትዮጵያውያን በሉዓላዊነት እና በሀገር ህልውና ጉዳይ የሚያሳዩት የማይበገር ጽናት የሚመነጨውም ከዚሁ የሕዝቦች ጥልቅ ውህደት እና ጠንካራ ማኅበራዊ መሰረት ነው።
እንደ ኢትዮጵያ ብዝሃ-ማንነት ባላቸው ሀገራት ውስጥ ሁሉም ወገን ድምፁ የሚሰማበት፣ ፍላጎቱ የሚከበርበት እና ድርድርን መሰረት ያደረገ የመግባባት ዴሞክራሲ መገንባት አማራጭ የሌለው መንገድ ነው።
ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ልዩነቶች በኃይል ሳይሆን በሃሳብ ልዕልና፣ በሰለጠነ ውይይት እና በመደራደር አቅም እንዲፈቱ በማድረግ ሂደት ውስጥ ይህ አካሄድ ቁልፍ ሚና ይጫወታል።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ሕዝብ የባህል እንዲሁም የቋንቋ ልዩነቶች የኢትዮጵያን አንድነት እና ልዕልና የሚያጠናክሩ ጽኑ መሰረቶች ናቸው።
ልዩነትን እንደ ጸጋ የመቀበል ባህል ይበልጥ ሲጎለብት እና የመግባባት ዴሞክራሲ በተቋማዊ ደረጃ ስር ሲሰድድ፣ የኢትዮጵያ ጽናት፣ ዘላቂ ሰላም እና አህጉራዊ ተደማጭነት ይበልጥ እየተጠናከረ ይሄዳል።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: