ግብጽ በዓባይ ተፋሰስ ላይ የምታራምደው ጸባጫሪነት እና የላይኞቹን ተፋሰስ ሀገራት መብት የሚጻረር አካሄድ ለእርሷም ሆነ ለቀጣናው እንደማይጠቅም ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ አሳሰቡ።
የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ እንዲሁም የውኃ ፖለቲካ ባለሙያው ፕሮፌሰር ያዕቆብ አርሳኖ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት አባል ባልሆኑበት እና ተጠቃሚ ባልሆኑበት የቅኝ ግዛት ሰነድ ሊገደዱ የሚችሉበት ምንም ዓይነት ዓለም አቀፍ ሕግ የለም ብለዋል።
በአንጻሩ ኢትዮጵያ ላለፉት 60 ዓመታት የተከዜን፣ ጣና በለስን፣ የአልወይሮን (አቦቦ) እንዲሁም ተመርቆ ሙሉ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘውን እና ቀጣናውን በመብራት ኃይል እያስተሳሰረ ያለውን የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶችን የገነባችው ሕዝቧን ከድህነት ለማውጣት እና የልማት መብቷን ለማረጋገጥ እንጂ ግብጽን ለመጉዳት አለመሆኑን አስገንዝበዋል።
ግብጽ የኢትዮጵያን የመልማት ጉዞ ማስቆም ባለመቻሏ አማፂያንን በማስታጠቅ ኢትዮጵያን ጨምሮ ምሥራቅ አፍሪካን ለማበጣበጥ እኩይ ሴራዎችን ማቀነባበሯን ፕሮፌሰር ያዕቆብ አስታውሰዋል።
ከዚህም በተጨማሪ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ውጥረት እንዲፈጠር ከ1961 ዓ.ም. ጀምሮ ታሪካዊ የጸረ-ኢትዮጵያ ሚና እንደተጫወተች ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ ግብጽ ይህንን አጥፊ አካሄድ በመተው ከተፋሰሱ ሀገራት ጋር በጋራና በፍትሐዊነት ሊያሠራ የሚችለውን የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ተቀብላ አሁን ወደተቋቋመው የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን እንድትቀላቀል ጥሪ ቀርቧል።
በውኃ ሀብቱ ላይ ያላቸውን ጥቅም ለማስተሳሰር እና በሰላም ለመሥራት የጸባጫሪነት መንገድን አስወግደው ትብብርን ሊመርጡ እንደሚገባ አመላክቷል።
በሜሮን ንብረት
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: