Search

"የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሪፎርም መለኪያ የዜጎች ተጠቃሚነት ነው" - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

ማክሰኞ መስከረም 19, 2019 149

የኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ሪፎርምና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ፣ ኢትዮጵያ ያላትን ከፍተኛ እምቅ አቅም በመጠቀም የዜጎችን ሕይወት በተጨባጭ ለመለወጥ ያለመ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የ2026ቱን የኢትዮጵያ ፋይናንስ ፎረም ዛሬ በዓድዋ ድል መታሰቢያ አስጀምረዋል።

ኢትዮጵያ እያካሄደችው ያለችው መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ሪፎርም እውነተኛ መለኪያ በውጭ ሀገራት በሚወጡ ሪፖርቶች ወይም በስታቲስቲክስ መረጃዎች ሳይሆን በዜጎች ሕይወት ውስጥ በሚመጣው ተጨባጭ ለውጥ የሚለካ መሆኑንም አብራርተዋል።

በተለይም አርሶ አደሮች፣ ወጣቶች፣ ሴት ሥራ ፈጣሪዎች፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች እንዲሁም ከትልልቅ ከተሞች ውጭ ያሉ ማህበረሰቦች የፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራ የሪፎርሙ ዋነኛ ማዕከል መሆኑን ጠቁመዋል።

አካታችነት የበጎ አድራጎት ሥራ ሳይሆን ሀገራዊ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ መሆኑን የጠቀሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በሦስተኛው ብሔራዊ የፋይናንስ አካታችነት ስትራቴጂ አማካይነት ተጠቃሚነትን ማሳደግ፣ የቤት ፋይናንስን ማስፋፋት፣ የካፒታል ገበያን ማሳደግ እና የዲጂታል መሰረተ ልማቶችን በመጠቀም የሥራ እድል ፈጠራን ማፋጠን አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያን የሚያጋጥሟትን ጊዜያዊ ፈተናዎች በማፈግፈግ ሳይሆን ተቋማዊ አቅምን በማጠናከርና ጠንካራ ሪፎርም በመተግበር በጽናት እንደምትሻገርም ገልጸዋል።

የመንግሥትና የግል ዘርፍ አጋርነትን በማጠናከር ለዜጎች ሰፊ እድል የሚፈጥርና ዘላቂ ብልፅግናን የሚያረጋግጥ የኢኮኖሚ ሥርዓት ለመገንባት የተጀመረው ጉዞ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።

በአሸናፊ እንዳለ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: