Search

ከአመለካከት ስብራት ወደ አህጉራዊ መሪነት፡ የኢትዮጵያ አዲስ የስኬት ምዕራፍ

ማክሰኞ መስከረም 19, 2019 131

ኢትዮጵያ ልዩነቶቿን የጥንካሬዋ ምንጭ ያደረገች ታላላቅ የተባሉ ተግዳሮቶችን በትጋት እና በጽናት የተሻገረች ድንቅ ሕዝብ ባለቤት ናት፡፡

ይህ ሕዝብ ባለፉት ዘመናት በርካታ ተደራራቢ ፈተናዎችን አልፎ ዛሬ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መጻፍ ጀምሯል፡፡

በሀገራችን ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው በዚህ አዲስ ምዕራፍ፣ በሀገር አቅም አይቻሉም ተብለው ተስፋ የተቆረጠባቸውን ግዙፍ መስኮች የመደመር መንግሥት በቆራጥነት ደፍሮ በመግባት ተጨባጭ ውጤቶችን ማስመዝገብ ችሏል፡፡

ለዓመታት "የእኛ አቅም አይፈቅድም" በሚል የተሳሳተ ዕሳቤ ትኩረት አጥተው የቆዩ የልማት፣ የኢኮኖሚ እና የመሠረተ ልማት ዘርፎች በመደመር አስተሳሰብ መሪነት አዲስ ሕይወት ዘርተዋል፡፡

ለአብነትም ኢትዮጵያ የምግብ እርዳታ ጥገኛ ናት፤ ስንዴንም ከውጭ ሳታስገባ መኖር አትችልም የሚለው የሰነበተ ዕሳቤ በበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል፡፡

ሀገራችን ከዝናብ ጥገኝነት ወጥታ፣ ጥቅም ላይ ያልዋሉ ሰፋፊ መሬቶችን በመስኖ በማልማት የምግብ ሉዓላዊነቷን ማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን የስንዴ ምርትን ወደ ውጭ ሀገራት መላክ ጀምራለች፡፡

በሌላ በኩል ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በይፋ ተመርቆ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ በመግባቱ የኢትዮጵያውያን የዘመናት ሕልም እውን ሆኗል፡፡

ግድቡ አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ ኃይል በማመንጨት የሀገራችንን የኤሌክትሪክ ፍላጎት ከመሸፈኑ ባሻገር ለጎረቤት ሀገራት የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ቀጣናዊ የኃይል እና የኢኮኖሚ ትስስርን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል፡፡

የውጭ ጫናዎች፣ የጂኦፖለቲካዊ መሰናክሎች እና የገንዘብ እጥረት ፕሮጀክቱን ለማስተጓጎል ቢሞክሩም በመንግሥት ቁርጠኝነት እና በሕዝቡ ያላሰለሰ ድጋፍ የማይቻለው ተችሎ ታላቁ የስኬት ማሳያ ሆኗል፡፡

በኢትዮጵያ የነበረው ሌላው ትልቅ ማነቆ ፕሮጀክቶች በቢሮክራሲ እና በዘገምተኝነት እየተጓተቱ በተቀመጠላቸው ጊዜ መጠናቀቅ አለመቻላቸው ነበር፡፡

በመደመር መንግሥት የተጀመረው የከተሞች ኮሪደር ልማት እና የቱሪዝም መስህቦች ግንባታ ይህንን የቆየ አሠራር ከስሩ ነቅሎታል፡፡

አዲስ አበባን ጨምሮ በበርካታ ከተሞች የተከናወኑት የኮሪደር ልማቶች ጥራታቸውን ጠብቀው በጥቂት ወራት ውስጥ መጠናቀቃቸው የሀገራችንን የፕሮጀክት ማስፈጸም አቅም ወደ አዲስ አህጉራዊ ደረጃ አሸጋግሮታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት በድፍረት የወሰደው አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የባንክ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስተሮች ክፍት የማድረግ ውሳኔ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከነበረበት መዋቅራዊ እስራት ያላቀቀ እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን የሚስብ ታላቅ እርምጃ ነው፡፡

እነዚህ በስትራቴጂያዊ ውሳኔ ላይ ተመስርተው ተጨባጭ ፍሬ ያፈሩ መስኮች የሚያሳዩት አንድ ታላቅ እውነታ ቢኖር ችግሩ የአቅም ሳይሆን የአመለካከት እና የቁርጠኝነት እንደነበር ነው፡፡

ጽኑው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአርቆ አሳቢ መሪነት ጋር ሲጣመር የማይሻገረው ፈተና እንደሌለ በተግባር ታይቷል፡፡

አይነኩም የተባሉ መስኮች መነካታቸው "እኛም እንችላለን!" የሚል አዲስ ሀገራዊ ኩራት እና በራስ መተማመንን ፈጥሯል፡፡

በዓይናለም ሃድራ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: