የአንድ ሀገር ትልቅነት መለኪያ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተቋቁማ ወደ ላቀ ከፍታ መሻገሯ ነው። ይህ እውነታ በዛሬው የዓለም ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ የሀገራትን ጽናት እና የመቋቋም አቅም ለመመልከት ጠቃሚ መነሻ ነው።
ዓለም በተደራራቢ የጂኦ-ፖለቲካ ውጥረቶች፣ በጸጥታ ችግሮች እና በመንግሥታት የመረጋጋት ፈተናዎች ውስጥ ባለችበት ወቅት፣ የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባሕር ቀጣናም ከዚህ ውስብስብ ሁኔታ ውጭ አይደሉም። በዚህ የተለያዩ ፈተናዎች ባሉበት ሁኔታ ኢትዮጵያ የሀገራዊ ጽናቷን እና የመቋቋም አቅሟን ለማጠናከር የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወኗን ቀጥላለች።
የዚህ ጽናት አንዱ ጉልህ መገለጫ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሂደት ነው። ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ ያጋጠሟትን የውጭ ጫናዎች እና የውስጥ ፈተናዎች በመቋቋም ፕሮጀክቱን እውን ወደ መሆን አሸጋግራለች። ከዚህ ባሻገር በተለያዩ የልማት ዘርፎች የተከናወኑ ትልልቅ ፕሮጀክቶችም የሀገራችንን የልማት አቅም እና የመፈጸም አቅም ለማጠናከር ያላቸው ሚና የጎላ ነው።
የሀገራዊ ጽናት ሌላው መገለጫ ደግሞ በፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ሂደቶች የታየው የውይይት እና የምክክር ባህል ነው። 6ኛው እና 7ኛው ጠቅላላ ምርጫዎችን ማካሄድ እና ሀገራዊ ምክክርን ማከናወን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ መሳተፍ እና መወያየት የሚቻልበትን ሂደት ለማጠናከር ከተደረጉ ጥረቶች መካከል ይጠቀሳሉ።
በዲፕሎማሲው መስክም ኢትዮጵያ የብሪክስ አባል በመሆን በዓለም አቀፉ የኢኮኖሚ እና ዲፕሎማሲ መድረክ ያላትን ተሳትፎ አስፋፍታለች። የሀገራዊ ጥቅምን ማስከበር፣ የውጭ ግንኙነቶችን ማስፋት እና ከተለያዩ አጋር ሀገራት ጋር ትብብርን ማጠናከር የውጭ ፖሊሲው ትኩረቶች መካከል ይጠቀሳሉ። በዚህ ረገድ የሀገራችን የመደራደር አቅም እና የዲፕሎማሲ ተሳትፎ ሀገራዊ ጥቅምን ከማስከበር ጋር ተያይዞ ወሳኝ ሚና አላቸው።
የባሕር በር ጥያቄም በዚሁ የሀገራዊ ጥቅም አውድ ውስጥ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ እና በሰላማዊ መንገድ እያነሣች ያለችው ጉዳይ ነው። ከቀይ ባሕር እና ከዓባይ የውኃ ሀብት ጋር የተያያዙ ጉዳዮችም በቀጣናዊ ትብብር፣ በውይይት እና በድርድር መፍትሔ የሚፈልጉ የሀገራዊ እና የቀጣናዊ ጥቅም ጉዳዮች ናቸው። ኢትዮጵያም ጉዳዮቹን በሰላማዊ የዲፕሎማሲ መንገድ ለማስኬድ አቅሟን እያጠናከረች ይገኛል።
በተቋማዊ አቅም በኩልም ሀገረ መንግሥቱን ለማስቀጠል፣ ለመጠበቅ እና የልማት ጉዞውን ለማስቀጠል የሚያስችሉ ዘመናዊ ተቋማትን የመገንባት ሂደት ተጠናክሯል። በጸጥታ፣ በደኅንነት፣ በኢኮኖሚ እና በቴክኖሎጂ ዘርፎች የሚታየው ተቋማዊ አቅም የሀገራችንን የመቋቋም አቅም ለማጠናከር ከሚያግዙ መሠረቶች አንዱ ሆኗል።
የኢኮኖሚ አቅም መጎልበትም በሀገራዊ ጽናት ውስጥ ወሳኝ ስፍራ አለው። በቅርብ ዓመታት የተካሄዱ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች፣ የምርት አቅምን ለማሳደግ የተደረጉ ጥረቶች እና የውጭ ምንዛሬ ምንጮችን ለማስፋት የተወሰዱ እርምጃዎች የኢኮኖሚውን የመቋቋም አቅም ለማጠናከር የታለሙ ናቸው። ኢኮኖሚያዊ አቅም መጎልበት በዲፕሎማሲ እና በጂኦ-ፖለቲካዊ ተሳትፎ የሀገርን አቅም ከሚወስኑ መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ ነው።
የኢትዮጵያ የቅርብ ዓመታት ጉዞ በተደራራቢ ፈተናዎች ውስጥ ተቋማዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ እና ማኅበራዊ አቅሞችን ለማጠናከር የተደረጉ ጥረቶች የታዩበት ሂደት ነው። የሀገር ጽናት የሚገለጸው ፈተና ባለመኖሩ ሳይሆን፣ ፈተናዎችን በመቋቋም ተቋማትን በማጠናከር፣ ሀገራዊ ጥቅምን በማስጠበቅ እና የልማት ጉዞን በማስቀጠል የመሻገር አቅም በመገንባት ነው። ይህም ኢትዮጵያ በሰላም፣ በልማት፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ እና በተቋማት ግንባታ ያላትን አቅም በቀጣይ ለማጠናከር የሚያስችላት መሠረት ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: