Search

ኢሬቻ ከገዳ ሥርዓት የሚመነጭ የእርቅ እና የሰላም መገለጫ ነው - ኦሮሚያ ኮሙኒኬሽን

ማክሰኞ መስከረም 19, 2019 97

የኢሬቻ በዓል ከገዳ ሥርዓት የሚመነጭ የእርቅ እና የሰላም መገለጫ በመሆኑ የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር ለሀገራዊ መግባባት ጉልህ ሚና እንዳለው የኦሮሚያ ክልል ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ገልጸዋል።

መስከረም 23 እና 24 ቀን የሚከበረውን የዘንድሮውን የሆራ ፊንፊኔ እና የሆራ አርሰዲ የኢሬቻ በዓል ምክንያት በማድረግ "ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ሀሳብ 51ኛው የጉሚ በለል ውይይት እየተካሄደ ይገኛል።

በኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት እና በክልሉ ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስተባባሪነት በሚካሄደው የውይይት መድረክ ላይ የተገኙት አቶ ሃይሉ አዱኛ፤ ኢሬቻ የሕዝቦች አንድነት፣ ሰላም፣ እርቅ እና መተሳሰብ ባማረ ሁኔታ የሚገለጽበት ታላቅ መድረክ መሆኑን አንስተዋል።

ኦሮሞ በገዳ ሥርዓት ሥር ጊዜን እና ቀንን በመቁጠር ትናንትን፣ ዛሬንና ነገን በማስላት አኗኗሩን የሚያስተካክልበት እና ሕይወቱን የሚመራበት ሥርዓት እንዳለው ኃላፊው ተናግረዋል።

ጊዜ የፈጣሪ ስጦታ መሆኑን በመገንዘብ፣ የሚመጣውን እና የሚያልፈውን ዘመን በማሰላሰል አዲሱን ዘመን ለሰው ልጅ የሚሰጠውን ፈጣሪን በኢሬቻ በመልካ ላለፈው በአንድነት እያመሰገኑ ለሚመጣው ደግሞ እንደሚጸልዩ ገልጸዋል።

የኢሬቻ በዓል በመልክ፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋም ሆነ በማንነት ልዩነት የማያደርግ እና ለሁሉም ክፍት የሆነ ዓለም አቀፋዊ መድረክ መሆኑን አቶ ኃይሉ አብራርተዋል።

በበዓሉ እሴቶች አክብሮት እና ለሀገር ፍቅር ያለው ትውልድ እየተገነባ መምጣቱን ያመላከቱት ኃላፊው በአሁኑ ወቅትም ይህንን የጥንት እሴት ወደሚገባው ቦታ በመመለስ ከራሱ አልፎ ለሀገር የሚያስብ ትውልድ እየተገነባ ይገኛል ብለዋል።

የዘንድሮው የኢሬቻ በዓልም የኢትዮጵያን ማንሰራራት አውጆ ወደ ታላቅ ድል እየተሸጋገርን ባለንበት ወቅት የሚከበር በመሆኑ ከፍተኛ ስሜት እና ትርጉም እንዳለው አንስተዋል።

ስለሆነም ሕዝቡ እሴቱን እያረጋገጠ ከሌሎች ብሔሮች ጋር ያለውን ወንድማማችነት በማጠናከር ወደ ከፍታ ለተጀመረው ጉዞ ተግቶ ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በዚህ በ51ኛው የጉሚ በለል መድረክ ምሁራን ስለ ኢሬቻ ምንነት፣ ሕግ፣ ሥርዓትና እሴት ሀገራዊ መግባባትን በመገንባት እና የኢትዮጵያን ከፍታ ወደፊት በማስኬድ ረገድ ያላቸውን ሚና በተመለከተ ዕውቀታቸውን እና ግንዛቤያቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ ቀርቧል።

በውይይት መድረኩ ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች እና ከተለያዩ ተቋማት የተወጣጡ ምሁራን በመሳተፍ ላይ እንደሚገኙ ኢዜአ ዘግቧል።

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: