Search

ኢትዮጵያን ትክክለኛ መስመር ያስያዘው የ'እንቁላሉ ከውስጥ መሰበር'

ማክሰኞ መስከረም 19, 2019 108

የ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ክስተት ነው።

ይህ ለውጥ በውጫዊ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት ወይም የመንግሥት መዋቅርን በማፍረስ የመጣ ሳይሆን፣ በሥርዓቱ ውስጥ በተፈጠረ ከፍተኛ ውስጣዊ ግፊት እና በሕዝባዊ ጥያቄዎች አማካይነት የተወለደ ታሪካዊ ሁነት በመሆኑ ከቀደሙት ልምዶች ልዩ ያደርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የለውጡን ተፈጥሮ ሲያስረዱ "እንቁላል ከውስጥ ሲሰበር ሕይወት፣ ከውጭ ሲሰበር ደግሞ ሞት ነው፤ ኢሕአዴግም ከውጭ ተሰብሮ ከሚሞት ከውስጥ ሰብረን ሕይወት እንዘራበታለን" ማለታቸው ይታወሳል።

ይህ ጥልቅ ተምሳሌታዊ ንግግር እንደሚያስገነዝበው፣ የለውጥ ሂደት ከውስጥ ሲጀምር የቆዩ የመልካም አስተዳደር እና የፍትሕ ስብራቶችን እያረመ አዲስ ሕይወትን እና ተቋማዊ ብቃትን ይወልዳል።

በአንጻሩ በውጫዊ ኃይሎች ወይም በኃይል የሚጫን ለውጥ የሥርዓተ-አልበኝነትን እና የመፈራረስ አደጋን የሚያስከትል ነው።

በመሆኑም የለውጡ ዋነኛ ትሩፋት ኢትዮጵያ በገጠሟት ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እንዳትወድቅ ጠንካራ መዋቅራዊ ከለላ መሆን መቻሉ ላይ ይገኛል።

የለውጡ መጀመሪያ ዓመታት፣ በተለይም ከ2010 ዓ.ም እስከ 2012 ዓ.ም የነበረው ጊዜ ኢትዮጵያ በርካታ ውስብስብ አካባቢያዊ ግጭቶች፣ የዜጎች መፈናቀል እና የፖለቲካ አለመረጋጋት ያጋጠማት ከባድ ምዕራፍ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም የተደቀኑት የሰሜኑ ግጭት፣ የውጭ የኢኮኖሚ ማዕቀቦች እና የህልውና አደጋዎች የትኛውንም ሀገር ሊያፈራርሱ የሚችሉ ጽኑ ፈተናዎች ነበሩ።

ሆኖም ይህን ሁሉ ከባድ ፈተና አልፎ ዛሬ ላይ መድረስ የተቻለው ለውጡ ከተነሳበት ትክክለኛ የሕዝብ ጥያቄ እና ከቆመበት ጽኑ ሀገራዊ ዓላማ ማዕዘን ዝንፍ ባለማለቱ ነው።

የለውጡ መሪዎች እና መላው ሕዝብ ኢትዮጵያን የማዳን እና የማሻገር ጠንካራ ሀሳብ ላይ በመቆማቸው ፈተናዎቹ የለውጡን ጉዞ ከማስቆም ይልቅ አቅም ፈጥረውለታል።

በዚህም ለውጡ ኢትዮጵያ የገጠማትን የህልውና አደጋ በራሷ አቅም እና በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ብቃቷን ያረጋገጠችበት ትልቅ የታሪክ ምዕራፍ ሆኗል።

የእነዚህ ሁሉ ድሎች መሠረት የሆነው የመደመር እሳቤ በምዕራባውያን ወይም በባዕዳን የፖለቲካ ንድፈ-ሐሳቦች ላይ የተገለበጠ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ዘመናት የተሻገረ የማኅበራዊ ትስስር፣ የእርቅ እና የውይይት ባህል መሠረት ያደረገ ሀገር በቀል እይታ ነው።

ይህ እሳቤ የሕዝቦችን ባህላዊ የእርቅ እሴቶች ከዘመናዊ የፖለቲካ አሠራር ጋር በማጣመር የተፈጠሩ ቁስሎችን ለማከም አስችሏል።

በአሁኑ ወቅት ጥልቅ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር እየሠራ የሚገኘው የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን የዚሁ የመደመር እሳቤ አካል ሲሆን፣ የቆዩ የፖለቲካ ቅራኔዎችን በሰላማዊ ውይይት ለመፍታት እና የጽኑ ሰላም መደላድል ለመጣል መንገዱን ክፍት አድርጓል።

የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ በውጫዊ ጥገኝነት እና በውስጣዊ ስብራት የተያዘችውን ኢትዮጵያ በራስ አቅም እና ሁለንተናዊ ሉዓላዊነት መሰረት ላይ ያቆማት የታሪክ ሽግግር ነው።

ይህ የለውጥ ጉዞ እና ያለፋቸው ከባድ ፈተናዎች ለመጻኢዋ ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ጽናት እጅግ ጠንካራ መሠረት መጣሉን በተጨባጭ ማሳያዎች ማረጋገጥ ይቻላል።

በግብርናው ዘርፍ ለዘመናት የነበረውን የምግብ እርዳታ ጥገኝነት በመስበር ከ33 ሚሊዮን ቶን በላይ ስንዴ የማምረት አቅም ላይ ራስን የመቻል ራዕይ ዕውን እየተደረገ ይገኛል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ-ግብር ከ65 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ዘላቂ የአየር ንብረትን ተቋቁሞ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት ለሚደረገው ጉዞ ጽኑ መሰረት ተጥሏል።

ከዚህም ባሻገር በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ አማካይነት የተካሄደው የውጭ ምንዛሬ ፖሊሲ ማሻሻያ፣ የፋይናንስ ዘርፍ ማዘመኛዎች እንዲሁም የኢንቨስትመንት ምህዳር መስፋፋት የኢትዮጵያን የማክሮ-ኢኮኖሚ መሠረት እያጠናከሩት ይገኛሉ።

ይህ የኢኮኖሚ አቅም ከዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ትግበራ ጋር ተዳምሮ ዘመናዊ አሠራርን በየዘርፉ እያስፋፋ ነው።

ከዚሁ ጎን ለጎን ዘመናዊ ከተሞችን ለመገንባት የተጀመረው የኮሪደር ልማት፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት እና የዲፕሎማሲ አድማስን በማስፋት የተገኘው የብሪክስ አባልነት የኢትዮጵያን የወደፊት ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት እና የተቋማት አቅም በተግባር ያረጋገጡ ናቸው።

ከእርዳታ ጥገኝነት ወደ ምርታማነት፣ ከፖለቲካ ግጭት ወደ ሰላማዊ ውይይት፣ ከፋይናንስ መዛባት ወደ ጠንካራ የማክሮ-ኢኮኖሚ መሠረት የተደረገው ይህ ሽግግር፣ ለመጻኢዋ ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት የማይናወጥ መደላድል ጥሏል።

ኢትዮጵያ በጽናቷ የጀመረችውን የለውጥ መስመር አጠናክራ በመቀጠል፣ የገጠሟትን ፈተናዎች ወደ እድል በመቀየር የታሪኳን ምዕራፍ በድል፣ በልማት እና በብልፅግና ማደሷን ትቀጥላለች።

በለሚ ታደሰ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: