የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ያዘጋጀው እና የኢትዮጵያን የ50 ዓመታት የሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ምርምር፣ ኢኖቬሽንና ዲጂታላይዜሽን ጉዞ እንዲሁም ያለፉት 5 ዓመታት የትግበራ ስኬቶችን የሚያሳይ ብሔራዊ ጉባኤ መካሄድ ጀምሯል።
በዚህ ጉባኤ ላይ የተለያዩ ተቋማት ሚኒስትሮች፣ የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የቀድሞ አመራሮች፣ የግሉ ዘርፍና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ኢትዮጵያ በ1968 ዓ.ም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ኮሚሽንን በማቋቋም በዘርፉ ለ50 ዓመታት በርካታ ሥራዎችን መሥራቷ በጉባኤው ተነስቷል።
የትምህርት ሚኒስትሩ ፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ በርካታ ውጤቶችን ማምጣቱን ጠቅሰው አሁንም ከዲጂታል ዘርፉ በተጨማሪ በባዮ እና ስፔስ ኢኮኖሚ ላይ የሚሠራው ሥራ ሊጠናከር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም በትምህርት ዘርፉ የቴክኖሎጂ እና የዲጂታል ውጤቶችን ተግባራዊ በማድረግ ትውልዱ ብቁ እና ተወዳዳሪ እንዲሆን እየተሠራ መሆኑን አብራርተዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባለፉት 50 ዓመታት ኢትዮጵያ በቴክኖሎጂ ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወኗን ጠቁመዋል።
በተለይም ባለፉት አምስት ዓመታት ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት ቴክኖሎጂን ከማላመድ አልፎ ወደ መፍጠር መሸጋገር መቻሉን አንስተዋል።
በእነዚህ ዓመታት በዲጂታል ቴክኖሎጂ ውጤቶች ሕዝቡን ተጠቃሚ ማድረግ የተቻለበት፣ ትውልዱን ያዘጋጀንበት እና አገልግሎቶችን በቀላሉ ተደራሽ ያደረግንበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ለዘርፉ ምቹ አሰራሮች የተዘረጉበት፣ የሰው ሰራሽ አስተውሎት የዳበረበት፣ የጥናትና ምርምር ሥራዎች መሬት የወረዱበት እና የስታርትአፕ ሥራዎች ይበልጥ እንዲጠናከሩ በአዋጅ ጭምር የታገዙ ተግባራት መከናወናቸውን በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ጠቅሰዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ለዘርፉ ሰፊ መሠረት የጣለ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030ም የዲጂታል እና ቴክኖሎጂ ተግባራት ይበልጥ እንደሚጠናከሩ አመላክተዋል።
ኢትዮጵያ የሰው ሰራሽ አስተውሎትን ጨምሮ በተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች ንቁ ተሳታፊ መሆኗን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ የሠለጠነ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድም ተጨባጭ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ሥራ ስምሪት እና ቴክኖሎጂ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብቷን ለማሳደግ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ማድረጓ ውጤት እያመጣ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
ምክር ቤቱም የኢትዮጵያን የዲጂታል ጉዞ የሚያጠናክሩ አዋጆችን በማጽደቅ እና የተፈጻሚነታቸውን ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
በአባዲ ወይናይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: