Search

ለኢትዮጵያ ቱሪዝም እና ትምህርት ዘርፍ ትልቅ አቅም ያለው ዓለም አቀፍ ላቦራቶሪ ሥራ ጀመረ

ማክሰኞ መስከረም 19, 2019 133

የኢትዮጵያን የቱሪዝም እና የትምህርት ዘርፍ በሳይንሳዊ ግኝቶች ከፍ ለማድረግ የሚያስችል፣ ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የምርምር ላቦራቶሪ በአዲስ አበባ በይፋ ሥራ መጀመሩን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን አስታውቋል።

“ፓሊዮኢትዮፕስ” (PaleoEthiopse) የተሰኘው ይህ ዓለም አቀፍ የምርምር ላቦራቶሪ፣ በኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን እና በፈረንሳይ ብሔራዊ የሳይንስ ምርምር ማዕከል ትብብር የተቋቋመ ነው።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር አቶ ኤሊያስ ሽኩር፣ የላቦራቶሪውን ሥራ መጀመር አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ማዕከሉ የሚያመነጨው አዳዲስ የሳይንስ ግኝቶች ለሀገር ውስጥ እና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ እንደሚተዋወቁ ገልጸዋል። ይህ ሂደት የኢትዮጵያን የቱሪዝም መዳረሻዎች ተወዳዳሪነት ከማሳደግ ባለፈ፣ የትምህርት ዘርፉን እውቀት በማበልጸግ ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።

ፈረንሳይ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያን ታሪካዊ እና ባህላዊ ቅርሶች በመጠበቅ እና በመንከባከብ ላደረገችው ተሳትፎ፣ ይህ ላቦራቶሪ ቀጣይ የትብብር ምዕራፍ አካል ነው ተብሏል።

በኢትዮጵያ የፈረንሳይ ኤምባሲ ምክትል አምባሳደር ጁሊያን ቮይቶሪይ በበኩላቸው፣ የሁለቱ ሀገራት ተመራማሪዎች በፓሊዮንቶሎጂ፣ በአርኪዮሎጂ እና በቅርስ ጥናት ዘርፎች ላለፉት ዓመታት በጋራ ሲያከናውኑት የነበረው ስኬታማ ትብብር፣ ላቦራቶሪውን መሠረት ጥሎ ማለፉን አስታውሰዋል።

ይህ ላቦራቶሪ ለወጣት ኢትዮጵያውያን እና ፈረንሳውያን ተመራማሪዎች ዘመናዊ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን እና የምርምር ስልቶችን የሚለማመዱበት፣ የእውቀት እና የልምድ ልውውጥ የሚያደርጉበት ዓለም አቀፍ መድረክ ሆኖ ያገለግላል።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣንን የጥናት እና ምርምር አቅም በከፍተኛ ደረጃ ከማሳደጉም በላይ፣ በላቁ የላቦራቶሪ ትንተናዎች አማካኝነት የተቋማቱን ሳይንሳዊ ተአማኒነት እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ይጠበቃል።

በብሩክታዊት ተገኝ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: