በሀገር አቀፍ ደረጃ ለሁለተኛ ጊዜ እየተካሄደ በሚገኘው በኢትዮጵያ የፋይናንስ ፎረም (Ethiopian Finance Forum 2026) ላይ ይፋ የተደረገው ይህ ፎረም፣ የሀገራችን ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት እና የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ መሠረት የሆነውን የፋይናንስ ዘርፍ ከሳይበር ጥቃት የመጠበቅ እና አይበገሬ የዲጂታል ፋይናንስ ሥነ-ምኅዳር የመፍጠር ዓላማ ያለው ነው።
የፎረሙን መመሥረት አስመልክቶ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ክብርት ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ክቡር ዶ/ር እዮብ ተካልኝ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ፎረሙ ባለፈው ሰኔ 2018 ዓ.ም የጸደቀውን የቁልፍ መሠረተ ልማቶች የሳይበር ደኅንነት አዋጅን መሠረት በማድረግ፣ በዘርፉ የሳይበር ደኅንነት እርምጃዎችን በመከታተል ክፍተቶችን እና የአሠራር ማነቆዎችን የሚፈታ ፎረም እንደሆነ ተገልጿል።
በምሥረታው መርሐ ግብር ላይ ማብራሪያ የሰጡት የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስታደር ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግሥት ሃሚድ፣ ፎረሙ በሀገራችን የፋይናንስ ዘርፍ ላይ የሳይበር ጥቃቶች ሲደርሱ መረጃ የምንለዋወጥበት እና ሊደርሱ የሚችሉ የሳይበር ጥቃቶችን በጋራ የምንከላከልበት ነው ብለዋል።
ዋና ዳይሬክተሯ አክለውም፣ ሀገራዊ እና ዘርፍ ተኮር የሳይበር ደኅንነት ፖሊሲዎች እና ሕጎች አተገባበር ላይ የሚያጋጥሙ ማነቆዎችን በመምከር የመፍትሔ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ፎረሙ ጉልህ ሚናን ይጫወታል ብለዋል።
የዘርፉን የሳይበር ደኅንነት አቅም የሚፈታተኑ ዋና ዋና ችግሮች በጥናት እንዲፈቱ አቅጣጫ ለማስቀመጥ፣ በዘርፉ ያሉ መልካም ልምዶችን እና ዓለም አቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማስፋት ፎረሙ እንደሚሰራም ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) በበኩላቸው ባደረጉት ንግግር፣ የሳይበር ደኅንነት ጉዳይ ለሀገራችን የፋይናንስ ዕድገት፣ በተለይም የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቱን ደኅንነት ከማረጋገጥ አኳያ ቁልፍ አጀንዳ መሆኑን አስገንዝበዋል።
የደንበኞችን አመኔታ ለማሳደግ፣ የፋይናንስ አካታችነትን (Financial Inclusion) ለማፋጠን እና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትን ለማረጋገጥ የተቋማት የሳይበር ደኅንነት አቅም ግንባታ ወሳኝ መሆኑን ያነሱት ገዥው፣ ሁሉም የፋይናንስ ሴክተር አመራሮች በፎረሙ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ እና የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ጥሪ አድርገዋል።
ፎረሙ በኢመደአ እና በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በጋራ ሰብሳቢነት የሚመራ መሆኑን እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተቋማት በፎረሙ ላይ በአባልነት እንደሚሳተፉ ከኢመደአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: