Search

'በጠጠር የማትታወከዋ ውቅያኖስ'፡- ኢትዮጵያ

ማክሰኞ መስከረም 19, 2019 146

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ጎረቤቶቻችን ኩሬና ሐይቅን መለየት ያስፈልጋቸዋል፤ ኢትዮጵያ በትንንሽ ጠጠር አትታወክም፣ አትበተንምም” ይላሉ።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል ኢትዮጵያ አሁን የደረሰችበት ጥንካሬ በምንም በጊዜያዊ ፈተና የማይናወጥ መሆኑንን የሚያሳይ ነው።

ኢትዮጵያ የሚያጋጥሟትን የፖለቲካ እና የደኅንነት ፈተናዎች በዘላቂነት ለመፍታት ከምንም በላይ ለሰላማዊ ውይይት እና ለዲፕሎማሲያዊ አማራጮች ቅድሚያ በመስጠት ትሠራለች።

መንግሥት ዘላቂ ሰላምን ለማስፈንና የኃይል አማራጮችን ለማስቀረት ሲል ሁሉን አቀፍ የውይይት መድረኮችን ለማመቻቸት ዘወትር ዝግጁነቱን አሳይቷል።

ላለፉት ስምንት ዓመታት የተተገበረው የውጭ ጉዳይና የዲፕሎማሲ ፖሊሲ በዋናነት ባለብዙ ወገን ተሳትፎን በማጠናከር፣ ብሔራዊ ጥቅምን በማስከበር እና ቀጣናዊ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ትስስርን በማሳደግ ላይ ያተኮረ ነው።

ኢትዮጵያ የብሪክስ (BRICS) አባል መሆኗ እንዲሁም የትውልዶች ህልም የሆነው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በዚህ የዲፕሎማሲ እና የልማት ፅናት የተገኙ ትልልቅ ማሳያዎች ናቸው።

እነዚህ ስኬቶች የኢትዮጵያን ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት ወደ ላቀ ደረጃ አሸጋግረዋል።

በሀገር ውስጥ የሚስተዋሉ የሐሳብ ልዩነቶችን እና ግጭቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ከተወሰዱት ዐበይት እርምጃዎች መካከል የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መቋቋም ግንባር ቀደሙ ነው።

ኮሚሽኑ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር አጀንዳዎችን በመሰብሰብ 4 ሺህ ሰዎች የተሳተፉበትን ዋና ጉባኤ አካናውኖ ምክረ ሀሳቦችን አጠናቅሯል።

በሰሜን ኢትዮጵያ የተካሄደውን ግጭት በሰላም ለመፍታት የተደረገው የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መንግሥት ለሰላማዊ መፍትሔ ያለውን ቁርጠኝነት በተግባር ያረጋገጠበት ዐቢይ ምዕራፍ ነው። የሰላም ፍላጎቱንም ያረጋገጠበት ነው።

በቀጣናዊ የዲፕሎማሲ መስክም “የአፍሪካ ችግሮች በአፍሪካውያን መፍትሔ” በሚለው መርሕ መሠረት ከአጎራባች ሀገራት ጋር የሚነሱ አለመግባባቶች በንግግር እና በጋራ የመልማት ፍላጎት ላይ ተመስርተው እንዲፈቱ ጽኑ አቋም ተይዟል።

ሰላምን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር ጎን ለጎን የሰላም በሮችን ክፍት በማድረግ፣ መሣሪያ ያነሱ አካላት ወደ ሰላማዊ መንገድ እንዲመጡ የቀረቡ ጥሪዎች እና የተደረጉ የምህረት ውሳኔዎች የዚሁ በጎ ሂደት ማሳያ ናቸው።

ይህ ሁሉ የሰላም አማራጭ እየቀረበ ብሔራዊ ጥቅምን የሚነኩ ጉዳዮችን በንግግር አንፈታም የሚሉ ጸብ አጫሪዎች ቢኖሩም ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷና በግዛት አንድነቷ ላይ ፈጽሞ እንደማትደራደር ግልጽ ነው።

ለዚህም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ጎረቤቶቻችን ኩሬና ሐይቅን መለየት ያስፈልጋቸዋል፤ ኢትዮጵያ በትንንሽ ጠጠር አትታወክም፣ አትበተንምም” ያሉት።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ሰፊ እና ጥልቅ ውቅያኖስ መሆኗን ጠቅሰው፣ የጥፋት ኃይሎች የሰላምን ጥሪ በመቀበል እጃቸውን መሰብሰብ እንዳለባቸው በአጽንኦት አስገንዝበዋል።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በፈተናዎች ውስጥ አልፋ የመሻገር ታሪካዊ ጥንካሬዋን ጠብቃ፣ የሰላምና የልማት ጉዞዋን በጽናት አጠናክራ ትቀጥላለች።

በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: