Search

ቁጭት የወለደው ስኬት፡ የትልቅ ሀገር ታላቅ ርዕይ በተግባር

ማክሰኞ መስከረም 19, 2019 137

ታላቅ ርዕይ ያላት ሀገር የቱንም ያህል ፈተና ቢገጥማት ከችግሩ ስፋት ይልቅ ከፈተናው ማግስት የምትፈጥረው ዕድል የላቀ ይሆናል።

የሀገራት የታሪክ ጉዞ አልጋ በአልጋ አለመሆኑ እሙን ቢሆንም ልዩነቱ የሚፈጠረው ግን ተግዳሮቶችን ለመጋፈጥ በሚወሰደው ስትራቴጂያዊ እርምጃ ላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ይህንን ሲያብራሩ፣ “በአንድ ሰው ሕይወት ውስጥ ወይም በአንድ ሀገር ጉዞ ውስጥ መከራ፣ ችግር፣ ተግዳሮት አይፈጠርም አይባልም። ነገር ግን አንድ ችግር፣ አንድ መከራ፣ አንድ አጥቂ ነገር ሲፈጠር፣ ያንን ነገር ወደ ዕድል ለመቀየር እና ከዚያ መከራ ውስጥ፣ ከዚያ ችግር ውስጥ ዕድል ለማውጣት መሥራት ለሰው ልጅ እንዲሁም ለሀገር እጅግ ያስፈልጋል” በማለት የችግር ፈቺነት አቅምን መገንባት ለሀገር ወሳኝ መሆኑን አጉልተዋል።

ይህ ፈተናን ወደ ዕድል የመቀየር የኢትዮጵያ ብቃት በተግባር የታየው ዓለምን ባናወጠው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ነበር። ያደገው ዓለም ለአፍሪካ እና ለኢትዮጵያ የሰጠው ትንበያ እጅግ አስፈሪ እና ተስፋ አስቆራጭ ነበር።

ሆኖም ሀገራችን የውጭ ሀገራት የራሳቸውን ዜጎች ለማዳን ፊታቸውን ባዞሩበት ወቅት የውስጥ አቅምን መገንባት ብቸኛው የህልውና ዋስትና መሆኑን ተማረች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ታሪካዊ ክስተት ሲያስታውሱ፣ “እነሱ ክትባት ስላላቸው፣ መድኃኒት ስላላቸው መትረፍ እንደሚችሉ፤ እኛ ግን ክትባት በበቂ ማምረት ስለማንችል፣ መድኃኒት ማምረት ስለማንችል ልንቋቋመው የማንችል መከራ እንደመጣብን በስፋት ተናግረው ነበር። እና ያንን ጊዜ በምግብም በመድኃኒትም ራስን ለመቻል እንደ ዕድል መጠቀም አለብን የሚል አቋም ከመንግሥት ወስደን ነበር” ብለዋል።

ይህ አስገዳጅ ሁኔታ መንግሥት በሀገር ሉዓላዊነት ላይ ያለውን ትርጓሜ ወደ ኢኮኖሚያዊ እና መሠረታዊ ፍላጎቶች ራስን መቻል እንዲያሰፋው አድርጓል።

እውነተኛ ሉዓላዊነት የሕዝብን አንገብጋቢ ፍላጎቶች በራስ አቅም ከማሟላት ይጀምራል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተፈጠረባቸውን ጥልቅ ቁጭት ሲገልጹ፣ “ያ ጉዳይ የፈጠረው ቁጭት መድኃኒት ላይ በበቂ አምርቶ የራሱን ፍጆታ የማይሸፍን ሀገር፣ ልብስ በበቂ አምርቶ የራሱን ፍጆታ የማይሸፍን ሀገር፣ ምግብ በራሱ አምርቶ የራሱን ፍጆታ የማይሸፍን ሀገር እንደሀገር ሉዓላዊ ሀገር ነኝ ብሎ መቀጠል አይችልም” በማለት አስረድተዋል።

በዚህም ታላቅ ርዕይ መሠረት በምግብ ራስን ለመቻል “በበጋ መስኖ መሬት ጦም አይደር” በሚል የተጀመረው የስንዴ ልማት፣ ሀገርን ከምግብ አቅርቦት መስተጓጎል አደጋ የታደገና ፈጣን ውጤት ያመጣ ስትራቴጂ ነው።

በተመሳሳይ በጨርቃጨርቅ ዘርፍ ሰፊ ርቀት የተኬደ ሲሆን ይህም ችግሮችን ወደ ዕድል የመቀየሩ ሥራ ብሔራዊ አቅምን ለመገንባት የተደረገ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ መሆኑን ያሳያል።

ከዚህ ጎን ለጎን አስደናቂ ስኬት እየተመዘገበ ያለው በመድኃኒት አቅርቦት እና ምርምር ዘርፍ ነው። በዚህም ስምንት በመቶ ብቻ የነበረውን ዛሬ ኢትዮጵያ ለሀገር ውስጥ የሚያስፈልጋትን መድኃኒት አርባ አራት በመቶ ማምረት የቻለች ሲሆን በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ይህ አቅም ሃምሳ አምስት በመቶ እንደሚደርስ ይጠበቃል፡፡

ይህንን ራዕይ ለማስፋት የአርማወር ሀንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት (AHRI) የደረሰበት የላቀ የቤተ ሙከራ ደረጃ ትልቅ ማሳያ ነው። ተቋሙ በጂኖሚክስ፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ናሙናዎችን በሚይዝ ቤተ ሙከራ እና አይጦችን ለበሽታ ልየታና ለማዕድን ፍለጋ በማሰልጠን ያካበተው አቅም ወደፊት የራሷን ክትባት ለማምረት ለምታደርገው ጥረት ጠንካራ ሳይንሳዊ መሠረት ነው።

በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ብልጽግና እና የተሟላ ሉዓላዊነት የሚረጋገጠው ተግዳሮቶችን በማሸነፍና ራስን በመቻል ነው። የኮሮና ወረርሽኝ ሀገራችን በምግብ፣ በልብስና በመድኃኒት ራሷን እንድትችል ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።

ይህ የትልቅ ሀገርና የትልቅ ሕዝብ ታላቅ ርዕይ ከዳር የሚደርሰው በትጋት ብቻ ነው። በመሆኑም ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራ፣ ዘልቃና አድጋ እንድትኖር ያለው መፍትሔ ጥረን ግረን መሥራት ብቻ ይሆናል።

እንደ ሀገር ከችግር ውስጥ ዕድልን አውጥቶ በጽናት መሥራት መቻል የብልጽግና ጉዟችንን ማንም ሊያቆመው እንደማይችል ማረጋገጫ ነው።

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: