Search

የተለየ የፖለቲካ ሀሳብ መኖሩ ጠላትነት አይደለም፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ረቡዕ መስከረም 20, 2019 126

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሆነው በድጋሚ የተመረጡት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የተለየ የፖለቲካ ሀሳብ መኖሩ ጠላትነት አለመሆኑን ገለጹ።

ከንቲባዋ ይህንን ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንግሥት ምስረታና 4ኛው ዙር የከተማው ምክር ቤት የመክፈቻ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።

በንግግራቸውም የመረጧቸውንም ሆነ ያልመረጧቸውን የከተማዋ ነዋሪዎች እኩል አገልግሎትና ክብር የማግኘት መብት እንዳላቸው ገልጸው፤ “የተለየ የፖለቲካ ሀሳብ መኖሩ ጠላትነት አይደለም፤ በምንስማማባቸው ጉዳዮች ለጋራ ጥቅማችንና ለሀገራዊ ራዕያችን አብረን እንሰራለን፤ በምንለያይባቸው ደግሞ ልዩነቶቻችንን እያከበርን በሰለጠነ መንገድ እንወያያለን” ብለዋል።

አዲሱ የከተማዋ ምክር ቤት የፖለቲካ ብዝሃነትንና አሳታፊነትን ያረጋገጠ ስብስብ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ በአዲሱ ምክር ቤት 12 ፓርቲዎች፣ 23 ተፎካካሪ የፓርቲ አባላትና 1 ገለልተኛ እጩ መቀመጫ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል። አዲሱ ምክር ቤት 41 በመቶ ሴቶችና 40 በመቶ ወጣቶች የተወከሉበት አሳታፊ ስብስብ መሆኑንም አክለዋል።

በ2018 ዓ.ም. በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነዋሪዎች ያሳዩትን ንቁ ተሳትፎ ያመሰገኑት ከንቲባዋ፣ የተሰጠው ድምጽ ባለፉት ዓመታት ለተከናወኑ የልማት ስራዎች እውቅና የሰጠና ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ለመመለስ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት “አዲስ አበባን እንደ ስሟ አዲስ እናደርጋታለን” ብለው የገቡትን ቃል ከጠበቁት በላይ ማሳካት መቻላቸውን ገልጸው፣ በቀጣይም የተጣለባቸውን አደራ በእኩልነትና በታማኝነት ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

 

በመሐመድ ፊጣሞ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: