Search

ስልጣን የሕዝብ አገልጋይነት እንጂ የግል ጥቅም ማካበቻ አይሆንም፡- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ረቡዕ መስከረም 20, 2019 165

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስኬቱን በቁጥርና ወረቀት ሪፖርት ሳይሆን በዜጎች የዕለት ተዕለት ህይወት ላይ በሚመጣ ተጨባጭ ለውጥ ለመለካት ግብ ማስቀመጡን የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።

ከንቲባዋ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመንግሥት ምስረታና የ4ኛ ዙር የመክፈቻ ጉባኤ ላይ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት፣ ስልጣን የሕዝብ አገልጋይነት እንጂ የግል ጥቅም ማካበቻ አይደለም።

በቀጣዮቹ ዓመታት ሌብነትን እና ሙስናን የማይታገስ ጠንካራ ሥርዓት እንዘረጋለን ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ ከተማዋን የ"ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030" ራዕይ አካል በማድረግ ረገድ ሰፊ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።

የአገልግሎት አሰጣጡን ሙሉ በሙሉ ወደ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን በማሸጋገር ነዋሪውን ከእንግልትና ከቢሮክራሲ ውጣ ውረድ የሚታደግ የሪፎርም ሥራ በፍጥነት እንደሚቀጥል አመልክተዋል።

የነዋሪውን የዕለት ተዕለት የኑሮ ጫና ማቃለል የቀጣዩ አምስት ዓመታት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባዋ፣ በተለይም ህገ-ወጥ ደላሎችን እና አሻጥር ፈጣሪዎችን ከገበያው ሥርዓት በማስወጣት የተረጋጋ ማክሮ ኢኮኖሚ ለመገንባት መታቀዱን አብራርተዋል።

ከዚህ ጎን ለጎንም ዜጎች ከተረጂነት ተላቀው አምራች የሚሆኑበትን ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ ለወጣቶችና ለሴቶች ሰፊ የሥራ ዕድሎችን ማመቻቸት እንዲሁም አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችን ማበረታታት ዋነኛ የኢኮኖሚ ስትራቴጂ መሆኑን አስታውቀዋል።

በዚህም ከተማዋን እውነተኛ የብልጽግና ማዕከል ለማድረግ የተያዘው ራዕይ እውን እንደሚሆን አብራርተዋል።

 

በበረከት ሽመልስ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: