የኢትዮጵያን የሩዝ ልማት በቴክኖሎጂ ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል የ360 ሚሊዮን የጃፓን የን (375 ሚሊየን የኢትዮጵያ ብር) የድጋፍ ስምምነት በኢትዮጵያና በጃፓን መንግሥት መካከል ተፈረመ።
ስምምነቱን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፣ በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሺባታ ሂሮኖሪ እንዲሁም የጃፓን ዓለም አቀፍ የትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) የኢትዮጵያ ቢሮ ዋና ተወካይ ሂሮዩኪ ያኩሺ ተፈራርመውታል።
በስምምነቱ መሠረት የሚገኘው የፋይናንስ ድጋፍ ትራክተሮችን፣ የእህል መውቂያ ማሽኖችን፣ የሩዝ ማቀነባበሪያዎችን እና የመሬት ማዘጋጃ መሳሪያዎችን ጨምሮ ልዩ ልዩ የዘመናዊ ግብርና ማሽነሪዎችን ለመግዛትና ለማቅረብ የሚውል ይሆናል ተብሏል።
ይህ የቴክኖሎጂ ድጋፍ ከአፈር ዝግጅት እስከ ምርት ስብሰባና ማቀነባበር ያሉትን ሂደቶች በማቃለል፣ የሩዝ ምርትን ጥራት ከፍ ለማድረግ እና ከምርት ስብሰባ በኋላ የሚከሰተውን ብክነት በከፍተኛ ደረጃ ለመቀነስ ትልቅ ድርሻ እንደሚያበረክት ተጠቅሷል።
በስነ-ሥርዓቱ ላይ የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ፣ ግብርና የሀገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እድገት በማፋጠን፣ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥና የገጠሩን ማህበረሰብ የኑሮ ደረጃ በመለወጥ ረገድ መሠረታዊ ድርሻ እንዳለው አስረድተዋል።
መንግሥት በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመናዊ አሰራርን በመዘርጋት የአርሶ አደሩን ህይወት ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ መሆኑን ያነሱት ሚኒስትሩ፤ በሩዝ ምርት ሰንሰለት ላይ የሚደረገው ይህ የሜካናይዜሽን እርምጃ ምርታማነትን ከፍ ለማድረግ፣ የገበያ አቅምን ለማሳደግና ከውጭ ሀገራት የሚገባውን የሩዝ ምርት በጥቅል ለመተካት የተያዘውን ሀገራዊ ግብ የሚያፋጥን መሆኑን መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል።
አቶ አህመድ ሽዴ ለጃፓን መንግሥትና ህዝብ ላደረጉት የገንዘብ ድጋፍና ለረጅም ዘመናት ለዘለቀው አጋርነት ምስጋናቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ጃይካ በኢትዮጵያ የግብርና ክፍለ-ኢኮኖሚ ላይ ለሚያደርገው ያልተቋረጠ ድጋፍም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: