Search

የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል የሚከበርበት ቦታ የማፅዳት ሥነ ሥርዓት ተካሄደ

ሓሙስ መስከረም 21, 2019 88

የአዲስ አበባ ከተማ ፅዳት አስተዳደር ኤጀንሲ የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓልን ምክንያት በማድረግ "ኢሬቻ - ለሀገራዊ መግባባት!" በሚል መሪ-ቃል በዓሉ የሚከበርበትን ቦታ የማፅዳት ሥነ ሥርዓት አካሂዷል።

በመርሐ ግብሩ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አባ ገዳዎች፣ ሃደ ስንቄዎች፣ የፅዳት አምባሳደሮች፣ አርቲስቶች፣ ወጣቶች እና ልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል፡፡

በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ጀማሉ ጀንበር (ዶ/ር)፣ “የኢሬቻ በዓል የመሸጋገሪያ ወቅት የምናመሰግንበት ትልቁ የሀገራችን ሀብት ነው” ብለዋል።

አክለውም በዓሉ በዓለማችን ቀደምት ከሆኑት የሥልጣኔ እና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አመራሮች አንዱ የሆነው የገዳ ሥርዓት የሚገለጽበት፣ እንዲሁም የሰላም፣ የፍቅር እና የመተካካት አንጡራ ሀብታችን መሆኑን ገልጸዋል።

በሀገራችን በዓሉን ለመታደም የሚመጡ የቱሪስቶች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ያሉት ኃላፊው፣ ያለምንም ኮሽታ የሚከበር ታላቅ የሰላም በዓል በመሆኑ በአብሮነት ደምቆ በአንድነት የምናከብረው በዓል መሆኑንም አንስተዋል።

በዓሉን ለማክበር ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ እንግዶችን በደመቀ ሁኔታ ለመቀበልና ለማክበር የከተማው አስተዳደር እና ነዋሪው በቂ ዝግጅት ማድረጉንም ገልጸዋል።

የአዲስ አበባ ጽዳት አስተዳደር ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ደሴ በበኩላቸው፣ የሃይማኖትና በአደባባይ የሚከበሩ በዓላት ቦታዎችን በማፅዳት የከተማው ነዋሪዎች በመስቀል አደባባይ እና በሆረ ፊንፊኔ ስፍራዎች በጋራ በመሰማራት የሚያኮራ የጽዳት ሥራ ማከናወናቸውን ተናግረዋል።

በሆረ ፊንፊኔ ስፍራ የጽዳት ፕሮግራም ላይ የተሳተፉት የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም አብሮነትና አንድነት የኢትዮጵያውያን መገለጫና ምልክት ነው ብለዋል።

በዓሊ ደደፎ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: