Search

የአማራ ክልል ምክር ቤት ለሕዝብ ፍላጎት ቅድሚያ በመስጠት ለዴሞክራሲ ሥርዓት መዳበር ይሠራል፦ ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ

ሓሙስ መስከረም 21, 2019 121

የአማራ ክልል ምክር ቤት በመጪው የሥራ ዘመን የሕዝብን ፍላጎት ቅድሚያ በመስጠት፣ የሕግ የበላይነትን እና የዴሞክራሲ ሥርዓትን ለማጠናከር በቁርጠኝነት እንደሚሠራ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬ አስታወቁ።

የአማራ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው የመንግሥት ምሥረታ እና 7ኛ ዙር የምክር ቤት ጉባኤ፣ ወ/ሮ ፋንቱ ተስፋዬን የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ አድርጎ መርጧል።

አዲሱ የምክር ቤቱ የሥራ ዘመን ሕገ-መንግሥቱን መሠረት ያደረጉ ሕጎችን በማውጣት፣ ግልጽነትን በተላበሰ መልኩ የሕዝብን ችግሮች የሚፈቱ ረቂቅ ሕጎችን መርምሮ በማጽደቅ እና የአፈጻጸም ክትትል በማድረግ እንደሚቀጥል ዋና አፈጉባኤዋ ተናግረዋል።

"የምናወጣቸው ሕጎች የክልላችንን ሕዝብ ተሳታፊነት እና ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ይሆናሉ" ያሉት ዋነ አፈ ጉባኤዋ፣ በምክር ቤቱ ውሳኔዎች ውስጥ የሕዝብ ጥቅም እንዲረጋገጥ፣ የቋንቋ፣ የማንነት እና የሐሳብ ብዝኃነት እንዲከበር ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

የምክር ቤት አባላት ውክልናቸውን በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበው፣ በተለይ በስድስተኛው ዙር የታዩ የመራጭ ሕዝብን የማነጋገር ክፍተቶችን በመቅረፍ፣ ሕዝቡን በአካል በመቅረብ የመሠረታዊ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

አዳዲስ የምክር ቤት አባላት የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት ለመወጣት የምክር ቤት አባላት በአንድነት እና በትብብር ሊሠሩ እንደሚገባ በማሳሰብ፣ አዲሱ የሥራ ዘመን የሰላም፣ የልማት እና የስኬት እንዲሆን ተመኝተዋል።

በሳሙኤል ወርቃአያሁ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: