Search

በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የክልሉን ሰላም በማስፈን ክልሉን ለልማት የተመቸ ለማድረግ በቁርጠኝነት ይሠራል - አቶ አረጋ ከበደ

ሓሙስ መስከረም 21, 2019 114

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው የተመረጡት አቶ አረጋ ከበደ በሚቀጥሉት 5 ዓመታት የክልሉ መንግሥት በሰላም፣ በልማት እና በመልካም አስተዳደር የተጀመሩ ሥራዎች የበለጠ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የክልሉ መንግሥት የክልሉን ሰላም በማስፈን ለልማት የተመቸ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሠራም አስታውቀዋል።

የፀጥታ ተቋማት ከማንኛውም የፖለቲካ ተፅዕኖ ወጥተው የዜጎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ እና የክልሉን ሰላም ለማስፈን በትኩረት እንዲሠሩ ይደረጋል ብለዋል።

የሐሳብ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ እና በውይይት ለመፍታት ሰፊ ጥረት እንደሚደረግም ጠቁመው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግም በትኩረት እንደሚሠራ አመላክተዋል።

በክልሉ አጎራባች አካባቢዎች አብሮነትን በማጠናከር እና በማጎልበት ገዥ ትርክት ለመፍጠር የክልሉ መንግሥት አበክሮ እንደሚሠራ አስገንዝበዋል።

በወጣቶች የሥራ ዕድል ተጠቃሚነት፣ የዜጎች የልማት ተቋዳሽነት፣ ሀብት በሚፈጥሩ ዘርፎች ላይ በትኩረት እንደሚሠራም ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያስታወቁት።

ለአብነትም ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ቱሪዝም፣ ማዕድን፣ ቴክኖሎጂ እና ሌሎችም ዘርፎችን ለማሳደግ በትኩረት ይሠራል ብለዋል።

የፀጥታ ችግሩ በትምህርት ዘርፉ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ለመቀልበስ የተቀናጀ ሥራ እንደሚሠራም አመላክተዋል።

በሳሙኤል ወርቅአየሁ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: