Search

የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ እመርታዊ ዕድገት ለማስመዝገብ በትኩረት ይሠራል - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሐመድ

ሓሙስ መስከረም 21, 2019 124

የሶማሊ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፋ ሙሐመድ በክልሉ ምክር ቤት 7ኛ የሥራ ዘመን 1ኛ ዓመት 1ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ንግግር አድርገዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በንግግራቸው መጀመሪያ ላይ፣ ለተጣለባቸው ከፍተኛ አደራ እና እምነት የክልሉን ሕዝብ እና ምክር ቤት አመስግነው፣ የተጀመረውን የለውጥ እና የብልጽግና ጉዞ ይበልጥ ለማስቀጠል ቃል ገብተዋል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት ክልሉን ለማረጋጋት እና ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ከፍተኛ ጥረቶች ተደርገዋል። በተለይም ዘላቂ ሰላም እና ልማትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት አበረታች ውጤት ማስመዝገባቸው ተገልጿል።

ይህንን ሰላም ይበልጥ ማስፋት እና አስተማማኝ ለማድረግ በቀጣይም በትኩረት ይሠራል ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ። ለዚህም ከማኅበረሰብ መሪዎች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች እና ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር በቅርበት መሥራት እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።

በክልሉ የሕዝብን ተጠቃሚነት የሚያልቁ የልማት ተግባራት የመንግሥት ቀጣይ አቅጣጫ መሆናቸውን ያነሡት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ክልሉ ያለውን ሰፊ የተፈጥሮ ሀብት እና እምቅ አቅም በአግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል እመርታዊ ዕድገትን ለማፋጠን እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በተለይም የክልሉን የውስጥ ገቢ ማሳደግ፣ የፋይናንስ ሥርዓቱን ማዘመን እና የግል ባለሀብቱን ተሳትፎ ማበረታታት ለኢኮኖሚው ዕድገት ወሳኝ ሚና እንደሚኖራቸው አስገንዝበዋል።

መንግሥት ለወጣቶች ሰፊ የሥራ ዕድል በመፍጠር ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የሙያ እና ቴክኒክ ሥልጠናዎችን ማስፋት፣ የፈጠራ ሥራዎችን ማበረታታት እና የብድር አቅርቦትን ማመቻቸት ትኩረት የሚሰጣቸው ተግባራት እንደሚሆኑ አስታውቀዋል።

የግብርና ልማትን ማጠናከር የክልሉን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እና የኢኮኖሚውን መዋቅር ለመቀየር ዋነኛው መሣሪያ መሆኑን አጽንዖት ሰጥተዋል።

የሶማሊ ክልል ለአርብቶ አደር እና ከፊል አርብቶ አደር ማኅበረሰብ ሰፊ የግብርና እና የእንስሳት ሀብት አቅም እንዳለው ጠቅሰው፣ ይህንን ዘርፍ በቴክኖሎጂ በማገዝ ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚሠራ ተናግረዋል።

የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ማስፋፋት፣ የውኃ አማራጮችን ማበልጸግ እና የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ የግብርና አሠራሮችን መዘርጋት በቀጣይ ትኩረት የሚሰጣቸው ዐበይት ጉዳዮች መሆናቸውን ነው የጠቆሙት።

በክልሉ መልካም አስተዳደርን ማስፈን እና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ ለተጀመሩት የልማት እና የሰላም ሥራዎች ስኬታማነት ወሳኝ በመሆኑ የመንግሥት ተቋማት ለሕዝቡ ቀልጣፋ እና ፍትሐዊ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

የተጀመሩትን የልማት፣ የሰላም እና የብልፅግና ግቦች ማሳካት የሚቻለው መላው የክልሉ ሕዝብ በአንድነት እና በትብብር ሲቆም በመሆኑ መንግሥት ከሕዝብ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሠራም አረጋግጠዋል።

በቴዎድሮስ ታደሰ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: