የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሺዴ እና የብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከዓለም ባንክ የኦፕሬሽን ዘርፍ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ብጀርዴ እንዲሁም ከባንኩ የምሥራቅ እና ደቡባዊ አፍሪካ ቀጣና ምክትል ፕሬዝዳንት ንዲያሜ ዲዮፕ ጋር ዛሬ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት አቶ አሕመድ ሺዴ የዓለም ባንክ የበጀት ድጋፍን ጨምሮ ለኢትዮጵያ እያደረገ ላለው ቀጣይነት ያለው አጋርነት ምስጋና አቅርበዋል።
መንግሥት እያካሄደ ያለውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ፣ በሀገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ የታየውን ዕድገት፣ የንግድ አካባቢን ለማሻሻል የተወሰዱ እርምጃዎችን እና የግሉን ዘርፍ ልማት ለማጠናከር እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን በተመለከተ ሰፊ ገለጻ አድርገዋል።
የዓለም ባንክ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አና ብጀርዴ በበኩላቸው መንግሥት በኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳው በግሉ ዘርፍ የሚመራ ዕድገትን በማረጋገጥ እና የሥራ እድል ፈጠራን በማበረታታት ያስመዘገበውን ተጨባጭ ውጤትና ቁርጠኝነት አድንቀዋል።
አያይዘውም ተቋማቸው በአዲሱ የአጋርነት ማዕቀፍ ስር ለልማት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ጉዳዮች ለመደገፍና ወደ ተጠናከረ የግሉ ዘርፍ መር ዕድገት የሚደረገውን ሽግግር ለማገዝ ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።
ሁለቱም ወገኖች በ"ሚሽን 300"፣ በአግሪኮኔክት ኮምፓክት፣ በኢ-ሞቢሊቲ ፕሮግራም እና በውኃ ፎርዋርድ ኢኒሼቲቭ የትኩረት መስኮች ላይ ትብብራቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ተስማምተዋል።
ከዚህም በተጨማሪም ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን እና ውጫዊ ጫናዎችን የመቋቋም አቅሟን ለማሳደግ የሚያስችሏትን ተጨማሪ የፋይናንስ አማራጮች ማግኘት ስለሚኖርባት አስፈላጊነት፣ እንዲሁም የሕዝቡን ተጨባጭ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የአፈፃፀም ብቃትን ማሻሻል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በስፋት መክረዋል።
ይህ ውይይት በኢትዮጵያ እና በዓለም ባንክ መካከል ያለውን ጠንካራ አጋርነት፣ የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማራመድ እና ዘላቂና አሳታፊ የሆነ የግሉ ዘርፍ መር እድገትን ለማበረታታት ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋገጠ ነው።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: