በምሥራቅ አፍሪካ እና በዓባይ ተፋሰስ ጂኦፖለቲካ ውስጥ የግብፅ የውጭ ፖሊሲ ማዕከል ሆኖ የቆየው አግላይ የውኃ ፖሊሲ፣ የሌሎችን ልማት ከመግታት የመነጨ መዋቅራዊ ፍላጎት መሆኑ ተገለጸ።
ግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን የተፈረሙ እና ኢትዮጵያ በሕግም ሆነ በሞራል የማትቀበላቸውን የ1929 እና የ1959 ፍትሐዊ ያልሆኑ ውሎችን እንደ ብቸኛ ሕግ በመቁጠር፣ ኢትዮጵያ ከተፈጥሮ ሀብቷ እንዳትጠቀም ለማድረግ ለበርካታ አሥርት ዓመታት ያልፈነቀለችው ድንጋይ አልነበረም።
በጉንደት እና በጉራ የጦር ሜዳዎች ወራሪ ሠራዊቷ ሙሉ በሙሉ ከተደመሰሰ በኋላ ካይሮ የቀጥታ ወታደራዊ ፍልሚያን በመተው፣ ኢትዮጵያን በውክልና ጦርነት፣ በእጅ አዙር የኢኮኖሚ ማዕቀብ እና በሥነ-ልቦና ፕሮፓጋንዳ ለማዳከም ስትራቴጂ ነድፋ ስትንቀሳቀስ ኖራለች።
የዚህ የሤራ ድር ዋና መግለጫ ደግሞ የውስጥ ቀውሶችን ማቀጣጠል እና ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አማፂያንን በግልጽም ሆነ በምስጢር መደገፍ ነው።
የግብፅ የደኅንነት ተቋማት የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስ እና ልማቷን ለማስተጓጎል በተለያዩ ጊዜያት ለተነሱ የጽንፈኛ እና ታጣቂ ቡድኖች የገንዘብ፣ የመሣሪያ እና የሥልጠና ድጋፍ ሲሰጡ መቆየታቸው በቂ ማስረጃዎች ያሉት ሀቅ ነው።
በአውሮፓውያኑ 2013 በፕሬዝዳንት ሙሐመድ ሙርሲ መሪነት በካይሮ የተካሄደው እና በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ለዓለም ይፋ የሆነው የግብፅ ፖሊቲከኞች ስብሰባ ይህንኑ እውነት አደባባይ አውጥቶታል።
ይህ ሤራ በተግባር ተተርጉሞ በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ወቅት በአካባቢው ሰላም ለማደፍረስ ለተንቀሳቀሱ ታጣቂዎች የፋይናንስ እና የሥልጠና ድጋፍ ሲደረግ ቆይቷል።
ይህ አልበቃ ሲላት ኢትዮጵያን በጂኦፖለቲካዊ መንገድ ለመክበብ እና ለመጫን፣ በቀጣናው የሚገኙ ጎረቤት አካላትን እንደ መንደርደሪያ እና የስጋት ምንጭ ለመጠቀም ያላሰለሰ ጥረት አድርጋለች።
የኢትዮጵያን ትኩረት ለማዛባት እንዲሁም የወታደራዊ እና የደኅንነት አቅሟን ለመበተን በምሥራቅ አፍሪካ ቀንድ ሦስትዮሽ እና ብዙ ወገን ጥምረቶችን ለመፍጠር ሙከራ ስታደርግ ቆይታለች።
የእነዚህ ሁሉ እኩይ እንቅስቃሴዎች ማጠናከሪያ ሆኖ የሚያገለግለው የካይሮ የብዙኃን መገናኛ እና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ነው። በግብፅ የሚገኙ ጋዜጦች፣ የመንግሥት እና የግል የቴሌቪዥን ቻናሎች እንዲሁም በገንዘብ የሚደገፉ አክቲቪስቶች ነጋ ጠባ የኢትዮጵያን ስም ለማጠልሸት እና በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ የተሳሳተ ገጽታ ለመፍጠር ይረባረባሉ።
ከዚህም በላይ በኢትዮጵያውያን መካከል ብሔራዊ እና ሃይማኖታዊ ልዩነቶች እንዲሰፉ፣ ጥላቻ እንዲነግሥ እና የውስጥ አንድነት እንዲላላ ከፍተኛ በጀት መድባ ስትሰራ ቆይታለች።
ይህ ዘመቻ ከዲጂታል እና ከሳይበር ጥቃቶች ጋር ተጣምሮ የኢትዮጵያን ቁልፍ የመሰረተ ልማት ደኅንነት አስተዳደሮች እና የመረጃ ሥነ-ምህዳር ለማወክ ያለመ ነው።
የካይሮ ድርጊት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ቻርተር አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 4 የሚደነግገውን የሉዓላዊነት መከበር እና በውስጥ ጉዳይ አለመግባት መርሕ የሚፃረር ሲሆን፣ የዓለም አቀፍ የድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ሕግ የሚያዝዘውን ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የመጠቀም መብት የሚጥስ ህገ-ወጥ ድርጊት ነው።
ነገር ግን ይህ ሁሉ ዘመናት የተሻገረ የሤራ ድር እና ሩጫ የኢትዮጵያን የነጻነት እና የልማት መንፈስ ሊሰብረው አልቻለም።
ኢትዮጵያ ያጋጠማትን የፋይናንስ እገዳ በመቋቋም በራሷ ሕዝብ አቅም ታላቁን የሕዳሴ ግድብ ግንባታ አጠናቅቃለች። በዚህም ለምሥራቅ አፍሪካም የብርሃን እና የኃይል ምንጭ መሆን መቻሏን በተግባር አሳይታለች።
በተጨማሪም የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ (CFA) ወደ ሕግነት መቀየሩ የግብፅን የብቻ ባለቤትነት አስተሳሰብ ያፈረሰ ትልቅ የዲፕሎማሲ ድል ሆኖ ተመዝግቧል።
የካይሮ መሰሪ ፖሊሲዎች የኢትዮጵያውያንን ብሔራዊ ወንድማማችነት እና የልማት ቁርጠኝነት የበለጠ ከማጠናከር ባለፈ ፍላጎቷን ማሳካት አልቻሉም።
የካይሮን የተወሳሰበ የሤራ ድር እና የውክልና ጦርነት መገንዘብ የብሔራዊ ደኅንነታችን የመጀመሪያው መከላከያ ሲሆን፣ የውስጥ ልዩነቶቻችንን በውይይት እየፈታን፣ ብሔራዊ አንድነታችንን በማጠናከር እና ለኢትዮጵያ ልማት በአንድነት በመቆም የካይሮን እና አጋሮቿን መሰሪ ሴራ ማፍረስ የዘመኑ ታሪካዊ ኃላፊነት መሆኑን ኢትዮጵያዊ ሁሉ የሚገነዘበ እውነት ሆኗል።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: