Search

የቀይ ባሕር ጂኦፖለቲካ እና የኢትዮጵያ ቀጣናዊ የመልህቅነት ሚና

ሓሙስ መስከረም 21, 2019 152

ከዓለም ንግድ 80 በመቶ በላይ የሚሆነው በባሕር ማጓጓዣ የሚከናወን ሲሆን፤ ይህ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በጥቂት ጠባብ የውኃ መተላለፊያዎች ላይ የተመሰረተ ነው።

በእነዚህ መተላለፊያዎች ላይ መዘጋት ወይም መረበሽ ሲያጋጥም ዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ እጅግ አሳሳቢ ቀውስ ውስጥ ይወድቃል።

ከእነዚህም መካከል አውሮፓን ከእስያ በአቋራጭ የሚያገናኘው ቀይ ባሕር፣ ባብ ኤል-መንደብን እና የስዊዝ ካናልን አቅፎ የያዘው መስመር ዋነኛው የዓለም የንግድ ልውውጥ ማዕከል ነው።

በየዓመቱ እስከ 14 በመቶ የሚደርሰው የዓለም የባሕር ላይ ንግድ እና 30 በመቶ የሚሆነው የኮንቴይነር እንቅስቃሴ ይህንን መስመር ያቋርጣል።

በመሆኑም መስመሩ ለጥቂት ጊዜ እንኳ ቢዘጋ አጠቃላይ የዓለም አቀፍ አቅርቦት ሰንሰለት ይስተጓጎላል።

የቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ብቻውን የዓለም ገበያን የሚያንቀሳቅስ ሲሆን፤ ጂኦፖለቲካዊ ትርጉሙ ደግሞ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ የማሳደር አቅም እንዲኖረው አድርጎታል።

በዚህ ከፍተኛ የፖለቲካ ግለት እና የደኅንነት ስጋት በሚታይበት ቀጣና ውስጥ የሰላም እና የመረጋጋት ዋስትና ሆና የቆመችው ኢትዮጵያ ናት።

የአፍሪካ ቀንድ ተመራማሪው ዳንኤል ወርቁ ከኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአልሸባብ፣ በአልቃኢዳ እና በሁቲ አማጺያን የተፈጠሩ ተደራራቢ የደኅንነት ስጋቶችን በመመከት ረገድ ከፍተኛ የሞራል ልዕልና አላት።

በተለይም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ኅብረት የሠላም አስከባሪ ሠራዊት (አሚሶም) ውስጥ ኃላፊነት በመውሰድ አሜሪካውያን ትተውት የወጡትን ክፍተት በመሙላት ረገድ የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አስታውሰዋል።

የአፍሪካ ቀንድ የጂኦፖለቲካ ተንታኝ ፕሮፌሰር አሌክስ ደ ዋል "The Real Politics of the Horn of Africa" በሚል መጽሐፋቸው እንደገለጹት ኢትዮጵያ የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ እና የደኅንነት ማዕከል ናት።

በቀጣናው የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሀገራት የፖለቲካ ህልውና እና የደኅንነት መዋቅር ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በኢትዮጵያ የውስጥ መረጋጋት እና የኃይል የበላይነት ላይ የተንጠለጠለ ነው።

ከኢትዮጵያ ውጭ ይህን ተለዋዋጭ ቀጣና በዘላቂነት ማረጋጋት የሚችል ሌላ አካል የለም።

ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ሰላም እና ደኅንነት መረጋገጥ እንደ ዋና ሞተር የምትቆጠር ሀገር ናት።

በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ከአካባቢያዊ ተዋናይነት ባለፈ በአፍሪካ ቀንድ፣ በቀይ ባህር እና በሰፊው የመካከለኛው ምሥራቅ ደህንነት ላይ ቀጥተኛ አንድምታ ያላት የማይተካ ስትራቴጂካዊ አጋር ናት።

ኢትዮጵያ የቀጠናው የጀርባ አጥንት በመሆኗ፣ የኢትዮጵያ አለመረጋጋት መላውን ቀጠና ከፍተኛ የደህንነት ቀውስ ውስጥ እንደሚከተው የዘርፉ ተመራማሪዎች ይስማማሉ።

በሜሮን ንብረት  

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: