የየም ብሔረሰብ የ2019 ዓ.ም ዘመን መለወጫ የ"ሄቦ" በዓል በሳጃ ከተማ በከፍተኛ ድምቀት ተከብሯል።
"ሄቦ" ብሩህ ተስፋ፣ ነፃነት፣ ደስታ ማለት ሲሆን የዕርቅ፣ የፍትህና የአንድነት ማጎልበቻ የሆነ የየም ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ በዓል ነው።
በበዓሉ ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ፣ የየም ህዝብ ሌብነትና ልመናን የሚፀየፍ ብሎም በኢትዮጵያ ዘመናዊ የህክምና ስርዓት ከመጀመሩ በፊት ከተለያዩ ዕፅዋት ለሰውና ለእንሰሳት መድኃኒት በመቀመም የሚታወቅ ህዝብ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ ሀገር በቀል የመድኃኒት ቅመማ እውቀትና የመድኃኒት ለቀማ ስርዓት በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ እና ጥበቃ እንዲደረግለት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አፈ ጉባዔዋ ጠቁመዋል።
የየም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሽመልስ እጅጉ በበኩላቸው የሄቦ በዓል መንፈሳዊና ባህላዊ ይዘት ያለው መሆኑን ገልፀው፣ በዓሉ ከመስከረም 14 ጀምሮ በተለያዩ ስያሜዎች እንደሚከበር አብራርተዋል።
እንደ አቶ ሽመልስ ማብራሪያ፣ መስከረም 14 የሚከበረው "ካም ኬሳ" የዕርቅ ስርዓት ሲሆን፣ በቤተሰብ፣ በወዳጅና በዘመድ አዝማድ መካከል የተፈጠረ ግጭትና የቆየ ቂም በእርቅ ስርዓት አስፈጻሚ ሽማግሌዎች (ማግ) አማካኝነት የእርቀ ሠላም ስርዓት የሚፈፀምበት ዕለት ነው።
መስከረም 15 "ኢፍቱ" ደግሞ በብሔረሰቡ ዘንድ የነጻነት ቀን በመሆኑ የግልና የአካባቢ ፅዳት ዘመቻ የሚደረግበት ቀን መሆኑን ገልጸዋል።
በተጨማሪም መስከረም 16 "አሜቱ" የሄቦ በዓል ዋዜማ ተራርቆ የቆየ ቤተዘመድ ወደ ወላጅ ቤት የሚሰባሰብበት ዕለት ሲሆን፣ መስከረም 17 "ኢሶንሲ ፊና" ደግሞ በብሔረሰቡ የዘመን አቆጣጠር የሄቦ ክብረ በዓል ወይም አዲስ ዓመት የሚበሰርበት ቀን መሆኑን አቶ ሽመልስ አስረድተዋል።
የየም ብሔረሰብ "ቻሎ" የተሰኘ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ያለው፣ በሀገር በቀል መድኃኒት ለቀማ የሚታወቅና በርካታ የቱሪዝም መስህቦች ያሉት ህዝብ መሆኑን የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው፣ እነዚህን ውብ ባህላዊ እሴቶችና ብዝኃሃብቶች ለማስጠበቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሄኖክ ተሰማ
#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: