የአዲስ አበባ ከንቲባ በ2018 በተካሄደው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ አገር አቀፍ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች ዛሬ እውቅናና ሽልማት ሰጥተዋል።
ከንቲባ አዳነች በፌስቡክ ማኅበራዊ ትስስር ገፅ ባጋሩት መልዕክት፣ በፈተናው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገባችሁ ተማሪዎች እውቅናና ሽልማቱን ስንሰጥ፣ ታላቅ ደስታና ኩራት ይሰማናል ብለዋል።
ይህ ሥነ-ሥርዓት የውጤታችሁን ዋጋ እውቅና ለመስጠት ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎች ተማሪዎች ተስፋና መነሳሳት የሆናችሁበትን ሚና ለማጉላትም ነው ብለዋል።
ከንቲባ አዳነች በመልዕክታቸው፣ ውጤት በአጋጣሚ አይገኝም፤ ከግልጽ ዓላማ፣ ከትጋት፣ ጊዜን በአግባቡ ከመጠቀምና በጽናት ከመቀጠል የሚመነጭ ነው ብለዋል።
ዛሬ ያስመዘገባችሁት ስኬት የእነዚህ ጥረቶች ፍሬ ነው፤ ስለዚህ ይህ ክብር ለእናንተ ብቻ ሳይሆን፣ ለቤተሰቦቻችሁ፣ ለመምህራኖቻችሁና ለመላው የትምህርት ማኅበረሰብ የሚገባ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ነገር ግን ይህ ውጤት መድረሻ ሳይሆን የቀጣዩ ስኬት መነሻ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ከዚህ በኋላ የሚጠብቃችሁ የበለጠ ዕውቀት፣ ኃላፊነትና ትልቅ ዓላማ ነው ሲሉ አሳስበዋል።
አያይዘውም፣ ዛሬ ያሳያችሁትን ትጋት በማስቀጠል፣ ለራሳችሁ፣ ለማኅበረሰባችሁና ለሀገራችሁ የሚጠቅም ትውልድ እንድትሆኑ አደራ እላለሁ ብለዋል።
የከተማችን የ12ኛ ክፍል ውጤት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ያሉት ከንቲባዋ፤ ይህ ስኬት ለትምህርት ዘርፍ በሰጠነው ትኩረት፣ እንዲሁም በተማሪዎች፣ በመምህራን፣ በወላጆችና በአመራሩ የተቀናጀ ጥረት የተገኘ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ለተመዘገበው ለውጥ አስተዋጽኦ ላደረጉ ሁሉ ምስጋና አቅርበው፣ ውጤቱ ጥሩ ቢሆንም ከግቡ ገና አልደረስንም፤ የትምህርት ጥራትን የበለጠ ለማሻሻልና ለተማሪዎቻችን የተሻለ ዕድል ለመፍጠር በትብብር መሥራታችንን እንቀጥላለን ነው ያሉት።
በተለይ ለተማሪዎች ባስተላለፉት መልዕክትም፣ “ውድ ተማሪዎቻችን፣ የዛሬ ስኬታችሁን ወደ ነገ አስተዋጽኦ ቀይሩት፤ ዕውቀታችሁን ለራሳችሁ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ጥቅም አውሉት። የምትማሩት ለፈተና ብቻ አይደለም ለሀገር ግንባታ፣ ለማኅበረሰብ ለውጥና ለተሻለ ነገ ነው” ብለዋል።
አክለውም፣ “ዛሬ በሽልማት የቆማችሁበት መድረክ ነገ በኃላፊነት፣ በአገልግሎትና በታላቅ አስተዋጽኦ የምትቆሙበት መድረክ ይሁን። ሕልማችሁን አሳኩ፤ ችግር ሲመጣ አትደክሙ፤ የተሰጣችሁን ዕድል በትጋትና በታማኝነት ተጠቀሙበት” ብለዋል።
የእናንተ ስኬት የቤተሰቦቻችሁ ደስታ፣ የከተማችን ኩራትና የሀገራችን ተስፋ ነውና፤ እንደገና ለሁላችሁም እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉ መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: