Search

ከፈተናዎች በላይ ገዝፎ መቆም፦ የኢትዮጵያ የይቅርታ እና የጽናት ጉዞ

ሓሙስ መስከረም 21, 2019 84

ኢትዮጵያ በታሪክ አጋጣሚዎች ሁሉ የነጻነት፣ የጽናት እና የክብር ተሳሌ ሆና የዘለቀች ታላቅ ሀገር ናት።

ማርኮ የሚያስቀር ተፈጥሮአዊ መልክዓ ምድር፣ ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እና እጅግ ሰፊ አምራች የሰው ኃይል የታደለችው ሀገራችን፤ ዘመናትን የተሻገሩ የታሪክ ፈተናዎችን በጽናት በማለፍ የጽኑ መሠረት ባለቤትነቷን አስመስክራለች።

የኢትዮጵያ ታላቅነት በኃይል እና በውጊያ ሜዳ በሚመዘገብ ድል አድራጊነት ብቻ የሚለካ አይደለም።

ይልቁንም ሀገራችን በተለያዩ ጊዜያት ውስጣዊ እና ውጫዊ ፈተናዎች ሲያጋጥሟት የምታሳየው ሆደ ሰፊነት፣ የይቅርታ በሯን ለመክፈት የምታደርገው ጥረት እና ለሰላም ያላት የማይወላወል ጽናት የታላቅነቷ ዋና ማረጋገጫዎች ናቸው።

በተለይም የመደመር መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ለፖለቲካ ትርፍ ሲሉ ሀገርን አደጋ ውስጥ የሚጥሉ አጋጣሚዎች ቢፈጠሩም ኢትዮጵያ ከአደጋው በላይ ገዝፋ በመቆም ጽናቷን በተግባር አሳይታለች።

በታሪኳ ለደረሱባት በደሎች በሙሉ አፀፋውን በበቀል የመመለስ ዕድል እና አቅም እያላት ሀገራዊ አንድነትን እና የሕዝቦቿን የወደፊት እጣ ፈንታ በማስቀደም ሁልጊዜም ለሰላም ቅድሚያ ስትሰጥ ቆይታለች።

ይህንን ለይቅርታ እና ለሰላም ክፍት የመሆን ባሕሪ በግልጽ ከሚያሳዩት ታሪካዊ እርምጃዎች መካከል የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ተነፃፃሪ የሌለው ማረጋገጫ ነው። ኢትዮጵያ እያሸነፈችው የነበረውን ጦርነት በሰላም ስምምነት የቋጨችው ምን ጊዜም ለሰላም ቅድሚያ እንደምትሰጥ ለማሳየት ነው። 

በተጨማሪም የተደረጉ የፖለቲካ እስረኞች ምህረት፣ የትጥቅ መፍታት ሂደቶች እና የሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ስኬታማ ሥራ በሀገራችን ዘላቂ ሰላምን ለመገንባት የተወሰዱ ቁልፍ እርምጃዎች ናቸው።

ግጭቶች በኃይል ብቻ ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ በወንድማማችነት እና በይቅርታ መንፈስ እንደሚቋጩ ኢትዮጵያ ለዓለም አሳይታለች።

በምክክር የተቆጡ ሲረጋጉ፣ ያኮረፉ እና የተበደሉ ሲካሱ የሰላም ፍሬዎችን ማፍራት ተችሏል።

ኢትዮጵያውያን በችግር ጊዜ የሚደጋገፉ በደልን በይቅርታ አልፈው ለጋራ ዕድገት የሚቆሙ ታላቅ ሕዝቦች ናቸው።

ይህ ሕዝብ ትናንት የደረሰበትን ቁስል በበቀል ሳይሆን በትእግሥት እና በይቅርታ አልፎ፣ ዛሬ ላይ በትጋት በመሥራት ነገን ብሩህ የማድረግ ታላቅ ርዕይ ሰንቋል።

ይህ ርዕይ ደግሞ በመደመር እሴቶች እና በተጨባጭ የልማት ሥራዎች እየተፋጠነ ይገኛል።

የሀገራችን ታላቅነት በቆዳ ስፋቷ ብቻ ሳይሆን በልቧ ስፋት፣ ለይቅርታ ባላት ዝግጁነት እና ለሰላም ባላት ጽናት የተረጋገጠ ነው።

ኢትዮጵያ እና ሕዝቦቿ የትናንት በደሎችን በይቅርታ አልፈው የታላቅነት እና የልማት ራዕያቸውን እውን ለማድረግ በጥንካሬ ወደፊት መራመዳቸውን ይቀጥላሉ።

በሃና ምንዳሁን

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: