በጊዜ ሂደት በፖለቲካዊ ሁነቶች ምክንያት ከአሰብ ከተማ ተፈናቅለው በኮምቦልቻ ከተማ በአንድ ሰፈር ተሰባስበው የሚኖሩት የአሰብ የቀድሞ ነዋሪዎች የዓመታት ትዝታ እና ቁጭታቸውን ለኢቲቪ አጋርተዋል።
በአሰብ ከነበረው የኢትዮጵያ ወደብ ጋር በተያያዙ ሥራዎች እንዲሁም በተለያዩ የንግድ እንቅስቃሴዎች ላይ በመሰማራት ላባቸውን አፍስሰው ከተማዋን ያቀኑት እነዚህ ዜጎች፤ የአሰብ የማንነት ጉዳይ ለእነርሱ የሰሚ፣ ሰሚ ወሬ ሳይሆን በተግባር የኖሩት እና እስከዛሬም በደማቸው ያለ ኢትዮጵያዊነቷ ነው።
አሰብ ከየአቅጣጫው የሰውን ልጅ በፍቅር ስባ በወንድማማችነት ታኖር እንደነበር በማስታወስ፤ ኮምቦልቻን ጨምሮ ከወሎ እና ከሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች የተሰባሰቡ ኢትዮጵያውያን በአብሮነት ይኖሩባት እንደነበር ይናገራሉ።
ቀይ ባሕር እና የኢትዮጵያ ሕልውና የማይነጠል ቁርኝት እንዳላቸው ሲያስረዱም፥ “ቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ እና ለሕዝቧ ልቧ እና አዕምሮዋ ነው፤ ልብ እና አዕምሮ ከሌለ ደግሞ፣ የሰው ልጅ ሊኖር አይችልም” በማለት ይገልፃሉ።
የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄያችን እውን ሆኖ በሕገ ወጥ መንገድ የተነጠቅናትን የሀገራችንን ግዛት እና የኖርንባትን ምድር ዳግም ለመርገጥ እና የመጨረሻ ዕድሜያችንን እዚያው ለማሳለፍ ጓጉተናል ነው ያሉት።
በኮምቦልቻ በአንድ ሰፈር የተሰባሰቡት እነዚህ የአሰብ ማንነት ሕያው ምስክሮች ኢትዮጵያ ከአሰብም አልፎ ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ስትራቴጂያዊ ቁርኝት በተጨባጭ ማስረጃ የተደገፈ እና ሊካድ የማይችል እንደሆነ በልበ ሙሉነት ይናገራሉ።
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: