የዓባይ ወንዝ በዓለም ታሪክ ውስጥ የሥልጣኔ መገኛ እና የሰው ልጅ ታላላቅ ምዕራፎች የተጻፉበት የሕይወት መስመር ተደርጎ ቢወሰድም፣ የዚህ ታላቅ ወንዝ ዋነኛ ምንጭ የሆነችው ኢትዮጵያ በገዛ ወንዟ ላይ ባይተዋር እንድትሆን ሲደረግ የቆየበት ሂደት የተዛባ ትርክት እንዴት ታሪክን ሊያዛባ እንደሚችል ትልቅ ማሳያ ነው።
ከሁለት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በፊት በግሪኩ የታሪክ ጸሐፊ ሄሮዶቱስ የተሰነዘረው “ግብፅ የዓባይ ስጦታ ናት” የሚለው ብሒል፣ ወንዙን ከምንጩ በማላቀቅ ግብፅን ብቸኛ ባለቤት አድርጎ ለመቅረጽ መሠረት ጥሏል።
በጥንታዊው ዓለም የተፈጠረው ይህ የትርክት መዛባት በሕግ እና በፖለቲካዊ መዋቅር ውስጥ ሰርጎ በመግባት የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን ለመቅረጽ መንገድ የከፈተ ሲሆን፣ የወንዙን የላይኛው ተፋሰስ ሀገራት መብት የገፈፈው የ1929 የአንግሎ-ግብፅ ስምምነት እና የዓባይን ወንዝ ዓመታዊ ፍሰት ሙሉ በሙሉ በግብፅ እና በሱዳን መካከል ብቻ ያከፋፈለው የ1959 ስምምነት እንዲፈረሙ ምክንያት ሆኗል። እነዚህ ስምምነቶች 85 በመቶ ውኃ የምታመነጨውን ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ያገለሉ ነበሩ።
ይህ የተዛባ ትርክት ያስከተለውን ጥልቅ የዲፕሎማሲ ጫና አስመልክቶ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሲገልጹ "ላገኘሁት የዓለም መሪ ሁሉ ማስረዳት የሚከብደኝ 'ዓባይ የሚመነጨው ከኢትዮጵያ ነው' የሚለውን እውነታ ነው" ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ይህም የዓለም መሪዎች በአካዳሚክ ምርምሮች እና በመገናኛ ብዙኃን የተመገቡት መረጃ ዓባይን ከግብፅ ጋር ብቻ ያቆራኘ እንደነበር ያሳያል።
ግብፅ የዓባይን ጉዳይ "የህልውና ሥጋት" አድርጋ በመቅረጽ፣ ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው ሕዝቧ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ የምታደርገው መሠረታዊ የልማት ጥረት ቀጣናውን ወደ ቀውስ የሚመራ የደኅንነት ሥጋት አስመስላ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስታቀርብ ቆይታለች።
ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷ ፈተና ውስጥ እንዲገባ ከተደረጉባቸው መንገዶች አንዱ የውስጥ ሰላሟን ማወክ መሆኑ የአደባባይ ተግባሯ ነው።
ግብፅ የዓባይን ወንዝ በብቸኝነት ለመቆጣጠር በታሪክ ሂደት ውስጥ በርካታ ስልታዊ ማደናቀፊያዎችን የተጠቀመች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ስለ ዓባይ ውኃ ልማት እንዳታስብ ለማድረግ የውስጥ አለመረጋጋቶችን መደገፍ ዋነኛው ስልቷ ነበር።
በድንበሮች ዙሪያ የሚታዩ ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች እና ቀውሶችም ሀገራችን ለዘመናት የብጥብጥ እና የድህነት ሰለባ እንድትሆን ታላቅ ዕንቅፋት ሆነው ኖረዋል።
ነገር ግን የካይሮ ተንኮል እና የዘመናት ሴራ የኢትዮጵያን የማድረግ አቅምና ብሔራዊ ጽናት ሊገታው አልቻለም። የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን ተራ የውኃ ማከማቻ ፕሮጀክት ሳይሆን እውነተኛውን ታሪክ ለማስመለስ የተደረገ ታላቅ ብሔራዊ የሉዓላዊነት ማረጋገጫ ሆኗል።
ግብፅ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ላይ ባደረገችው ጫና ምክንያት ኢትዮጵያ የውጭ ብድር እንዳታገኝ ተደርጋ የኖረች ቢሆንም፣ ግድቡ በራሳቸው በኢትዮጵያውያን ተፈጥሯዊ አቅምና ቁርጠኝነት ተገንብቶ የነፃነት ምልክት ለመሆን በቅቷል።
የግድቡ መጠናቀቅ የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን የውኃ የበላይነት ሙሉ በሙሉ የሰበረ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ለምትሻው ቀጣናዊ ትብብር አዲስ በር ከፍቷል።
ታላቁ የሕዳሴ ግድብ በዓባይ ላይ የተሰራጨውን የዘመናት የተዛባ ትርክት በማምከን መሬት ላይ ያለው ተጨባጭ የኢትዮጵያ የማድረግ አቅም እውነት በድል አድራጊነት የቆመበት አዲስ የትውልድ ምዕራፍ መሆኑ ተረጋግጧል።
በለሚ ታደሰ
#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: