ኢሬቻ! ከትውልድ ወደ ትውልድ በክብር የተሸጋገረ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪን የሚያመሰግንበት፣ ሰላምን የሚያውጅበት፣ ይቅርታን የሚያወርድበት እና አንድነቱን የሚያበስርበት ታላቅ በዓል ነው። ኢሬቻ የሰው ልጅ ከተፈጥሮና ከፈጣሪው ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከወንድሙም ጋር የሚያደርገው ታላቅ የሰላም ውል ነው።
በኢሬቻ ሥርዓት ውስጥ ቂም አዝሎ፣ ጠብና ግጭት ፈጥሮ መገኘት በፍጹም አይፈቀድም። ወደ በዓሉ ስፍራ የሚያመራ ማንኛውም ሰው ከሥርዓቱ በፊት ይቅር የመባባል፣ ሰላምን የማስፈን ግዴታ አለበት። ይህ የሰላምና የዕርቅ ባህል ደግሞ የኢትዮጵያን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ለማጠናከር፣ የጋራ መግባባትን ለመፍጠርና ማህበራዊ ትስስርን ለማጥበቅ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
ኢትዮጵያ ታሪካዊውን ሀገራዊ ምክክር ባካሄደችበት ማግስት የሚከበረው የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል ደግሞ ልዩ አንደምታ አለው። በሀገራዊ ምክክሩ ከመላው ኢትዮጵያ የተወከሉ ተሳታፊዎች ተሰብስበው መክረዋል፤ የቀደመውን ቁርሾ ፈትቶ መጪውን የኢትዮጵያ ጊዜ ብሩህ ለማድረግ ብዙ ርቀት ሄደዋል።
ምሁሩና አርሶ አደሩ፣ የዕውቀትና የልምድ አቅማቸውን አስተባብረው፤ ሴቷና ወንዱ፣ የእኩልነትና የጋራ ተሳትፎ ድምጻቸውን አሰምተው፤ ወጣቱና አንጋፋው፣ የተስፋና የጥበብ ድልድይ ገንብተው፤ ሁሉም በየፊናው በተወከለበት በዚህ ታሪካዊ መድረክ፣ መፍትሔ አልባ መስለው ለዘመናት የተቀመጡ ውስብስብ ልዩነቶች ተመክሮባቸዋል። በዚህም ሀገራችን ኢትዮጵያ እውነተኛ የፈውስ ጉዞዋን በይፋ ጀምራለች።
ኢሬቻ ዕርቅ ነው! ኢሬቻ ሰላም ነው! በሀገራዊ ምክክሩ የተጀመረው የሕዝቦቿ የመደማመጥና የፈውስ ጉዞ በኢሬቻ የሰላም፣ የይቅርታ እና የአንድነት ዕሴት ተጠናክሮ ይቀጥላል።
የኢሬቻ ሰላማዊነትና የሀገራዊ ምክክሩ የጋራ መግባባት ተቀናጅተው ለኢትዮጵያ አዲስ የብሩህ ተስፋና የዘላቂ ወንድማማችነት ምዕራፍ ይከፍታሉ።
በዓይናለም ሀድራ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: