የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለኢሬቻ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ከንቲባዋ በዓሉን አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለኢሬቻ በዓል በሰላም አደረሳችሁ!
ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት!!
ኢሬቻ የፈጣሪ ጸጋና ለጋስነት የሚመሰገንበት፣ ከተፈጥሮ ጋር ቃል ኪዳን የሚታደስበት፣ የሰላም፣ የፍቅር፣ የይቅርታና የአብሮነት በዓል ነው።
የኢሬቻ በዓል ልክ ከክረምቱ ጭጋግ ወደ ፈካውና በአደይ አበባ ወደአሸበረቀው መስከረም መሸጋገርን እንደሚያበስር ነው።
ከተማችን በኢሬቻ በዓል አሸብርቃ፣ ከምንጊዜውም በላይ ለቱሪዝም ዘርፍ ዕድገትና ለእንግዳ ተቀባይነት የተመቸች፣ የሰላምና የውበት መገለጫ ሆና በደስታ ኢኮኖሚዋን እያነቃቃችበት ነው።
“ኢሬቻ ለሀገራዊ መግባባት" በሚል መሪ ቃል የሚከበረው የዘንድሮው በዓል በድምቀትና ባማረ ድባብ እንዲከበር ከተማችን አዲስ አበባ የተለያዩ የስነ-ጥበብና የኪነ-ጥበብ ዝግጅቶችን፣ ኮንሰርቶችን፣ የፓናል ውይይቶችን፣ የስፖርት ውድድሮችን፣ ፌስቲቫሎችን፣ የፎቶ ኤግዚቢሽኖችን እና የመሳሰሉትን አዘጋጅታ በዓሉ በከፍተኛ ድምቀት እንዲከበር እየተደረገ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ፣ የከተማችን ነዋሪዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እና ከውጭ ሀገር የሚመጡ ክቡራን እንግዶቿን ለመቀበል ዝግጅቷን አጠናቅቃ በትብብርና በላቀ መስተንግዶ ላይ ትገኛለች። በመሆኑም በዓሉ የሁላችን መድመቂያ፣ ለመዲናችን ጥልቅ የቱሪስት መስብ ፣ አቅምና ጸጋ፣ ለዓለም የሚያንጸባርቅ ልዩ መድረክ ነው።
ስለሆነም፣ ይህ የጋራ ኩራት የሆነው ድንቅ በዓል፣ መላው የከተማችን ነዋሪዎች ያካበቱትን የላቀ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል በተግባር በማሳየት፣ ከየአካባቢው የሚመጡ ወገኖቻችንን በክብር በመቀበል፣ በፍቅር እና በከፍተኛ የአብሮነት ስሜት በድምቀት እንዲከበር ጥሪዬን በአክብሮት አቀርባለሁ።
በድጋሚ እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ!
ትልቅ_ሀገር ትልቅ_ሕዝብ ታላቅ_ርዕይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: