መንገድ ስተው ከሀገራቸው በተቃራኒ ለቆሙ አካላት የሰላም በር አሁንም ክፍት መሆኑን አረጋግጠው፣ የኦሮሞ ጥያቄ ከእንግዲህ በጠብመንጃ አፈሙዝ ሳይሆን በሰላምና በትግሉ ባገኘው ነፃነት ብቻ የሚመለስ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለኢሬቻ በዓል ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሀገርን ከጠላትና ከባንዳ በመጠበቅ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።
በንግግራቸውም “እኔ ስጋ ብቻ ልብላ፤ እንስሳዬ ግን እንዳይነካ” የሚል ጠላትና ባንዳ ፊት ቆመን የሀገራችንን ጥቅም እናስከብራለን ባሉበት ወቅት፣ መንገድ ስተው ከሀገራቸው በተቃራኒ ለቆሙ አካላት የሰላም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም፣ “ኦሮሞ ‘ከሚያመሹበት የሚያድሩበት ቤት ይሻላል’ ብሎ እንደሚተርት አሁንም ፊታቸውን ወደ ሰላም ከመለሱ፤ የሰላም በር እንደተከፈተ ያለ መሆኑን ላረጋግጥላቸው እወዳለሁ” ብለዋል።
ኦሮሞ በትግሉ ነፃ መውጣቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከዚህ በኋላ በጠብመንጃ አፈሙዝና ከጠላት ጋር በመወገን የሚመለስ የኦሮሞ ጥያቄ ፈፅሞ እንደማይኖር በግልጽ አስረድተዋል።
ህዝቡ የኢሬቻን በዓል ሲያከብር እንደ እሴቱ አንድነትን አጥብቆ፣ እጁን ለሰላምና ለዕርቅ በመዘርጋት እንዲሁም ቀልቡን ወደ ይቅርታ በመመለስ ስላገኘው ነገር ፈጣሪን እያመሰገነ ያጣውን በትዕግስት እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርበዋል።
ልክ ትናንት ኦሮሞ በአባቶቹ ደምና አጥንት ኢትዮጵያን እንደገነባ ሁሉ፣ ዛሬም የኢትዮጵያን ስልጣኔ ዕውን ለማድረግ ባለው ዕውቀት፣ አቅምና ሀብት ከሌሎች ወንድም የኢትዮጵያ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ጋር በመሆን በግንባር ቀደምነት ኢትዮጵያን እንዲያፀና አሳስበዋል።
በጌቱ ላቀው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: