አንዳንድ በትሮች ከእንጨትነት ያለፈ ጥልቅ ትርጉም አላቸው፡፡
ከሚታየው ገጽታ በስተጀርባ ታላቅ ታሪክ እና ማኅበራዊ እሴት ይዘው ይገኛሉ፡፡
በኦሮሞ ባህል ውስጥ "ሲንቄ" የዚህ ጥልቅ ትርጉም ማሳያ ናት፡፡ ሀዳ ሲንቄ (የሲንቄ እናት) በእጇ የምትይዘው ይህች ቀጭን በትር የሴትን ክብር፣ መብት፣ ማኅበራዊ ተሳትፎ እና የሰላም ሚናን አጉልታ የምታሳይ ታላቅ ምልክት ናት፡፡
ሲንቄን ይዛ የምትታየው ሴት አንዲት ግለሰብን ብቻ አትወክልም፡፡ ይልቁንም የእናቶችን ድምፅ፣ የሴቶችን ክብር እና የማኅበረሰቡን የሰላም እሴት ተሸክማ የቆመች የሕዝብ ወኪል ናት፡፡
ይህች በትር በሠርግ ዕለት እናት ለልጇ የምታበረክታት ስጦታ ስትሆን ሴት ልጅ ወደ አዲስ ሕይወት ስትገባ መብቷ የተጠበቀ፣ ክብሯ ከፍ ያለ እና በማኅበረሰቡ ውስጥ ጸጋዋ የጎላ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሕያው ቃል ኪዳን ነው፡፡
ሲንቄ በገዳ ሥርዓት ውስጥ የሴቶች መብት መጠበቂያ ተቋም ሆኖ ያገለግላል፡፡ የገዳ ሥርዓት ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ሥነ ሥርዓታዊ ሕይወትን ሲያደራጅ ሲንቄ ደግሞ የዚህ ሥርዓት ዋነኛ አካል በመሆን የሴቶችን ማኅበራዊ ሚና ታረጋግጣለች፡፡
ማኅበራዊ ግጭት ሲነሳ፣ ሰዎች ሲቆጡ እና የጦርነት ድምፅ ሲሰማ ሲንቄን የያዙ እናቶች በመካከል ገብተው ግጭቱ እንዲቆም የሚጠይቁበት የዳበረ የሰላም ባህል አለ፡፡
በዚህ ጊዜ የሀዳ ሲንቄ ልዩ ኃይል ይገለጣል፡፡ እሷ ጦር ይዛ አትዘምትም፤ ጠመንጃም አታነሳም፤ ነገር ግን የያዘቻት ሲንቄ ከጦር መሳሪያ በላይ ኃያል ናት፡፡
ሌላውን ለማሸነፍ ሳይሆን ሰዎች እንዳይጎዱ፣ ደም እንዳይፈስስ እና ጥላቻ እንዳይስፋፋ በመካከል ትገባለች፡፡
በዚህ መልኩ ሀዳ ሲንቄ በሁለት የተጣሉ ወገኖች መካከል እንደምትቆም የሰላም ድልድይ ናት፡፡ ድልድይ መሆን ወገንተኛነትን ሳይሆን፣ ሁለቱን ዳርቻዎች ማገናኘትንና ማስታረቅን ያመለክታል፡፡ ግጭትን በግጭት ሳትመልስ፣ በማኅበራዊ ክብር እና በእናትነት ፍቅር ነገሮችን ወደ ሰላም ትመልሳለች፡፡
የሲንቄ ጽንሰ ሀሳብ ከግለሰብ መብት ተነስቶ ወደ ማኅበረሰብ ሰላም ይዘልቃል፡፡ የሴት መብት ሲከበር ቤተሰብ ይረጋጋል፤ ቤተሰብ ሲረጋጋ ማኅበረሰብ ሰላም ያገኛል፤ ማኅበረሰብ ሲረጋጋ ደግሞ አጠቃላይ ሰላም እና አብሮነት ይጠናከራል፡፡
በመሆኑም ሲንቄ የሴቶችን ክብር ከማኅበረሰቡ ጸጥታ ጋር የሚያስተሳስር ወርቃማ ባህላዊ እሴት ነው፡፡
ይህ የሀዳ ሲንቄ ክብር እና ሞገስ በጉልህ ደምቆ ከሚታይባቸው አጋጣሚዎች መካከል የምስጋና፣ የሰላም፣ የአንድነት እና የአዲስ ዘመን መጀመርያ የሆነው ታላቁ የኢሬቻ በዓል ዋነኛው ነው፡፡
በኢሬቻ ላይ ሲንቄን ይዘው በነጭ ባህላዊ ልብስ አሸብርቀው የሚሳተፉ እናቶችን ማየት የበዓሉን ውበት ከማድመቅ ባለፈ በእጃቸው ያሉት በትሮች የሴቶችን ክብር፣ የእናቶችን ድምፅ፣ የሰላም ጥሪን እና የማስታረቅ ባህልን ሕያው አድርገው ያሳያሉ፡፡
በሃና ምንዳሁን
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: