የዘንድሮው የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓል ባህላዊ እሴቱን እና ትውፊቱን ጠብቆ፣ በሰላም፣ በደስታ እና በልዩ ድምቀት ተከብሮ መጠናቀቁን ከንቲባ አዳነች አቤቤ አስታውቀዋል።
ከንቲባዋ የሆረ ፊንፊኔ ኢሬቻ በዓልን መጠናቀቅ አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት፣ ኢሬቻ የምስጋና፣ የሰላም፣ የፍቅር እና የአንድነት ሕያው መገለጫ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በዓሉ ከባህላዊ እሴቱ ባሻገር፣ የተለያዩ ሕዝቦች በፍቅር እና በወንድማማችነት የሚገናኙበት እንዲሁም የአብሮነት እና የመቻቻል እሴቶች የሚጎሉበት ታላቅ መድረክ መሆኑንም አብራርተዋል።
ይህንን መሠረት በማድረግም መላው ሕዝብ የኢሬቻን እሴቶች በተግባር በመግለጽ፣ አቅሙን አስተባብሮ እና አንድነቱን አጽንቶ ለኢትዮጵያ ሰላም፣ ለሀገራዊ መግባባት እና ለሁለንተናዊ ብልጽግና በጋራ እንዲተጋ ጥሪ አቅርበዋል።
በዓሉ በስኬት እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና ያቀረቡት ከንቲባ አዳነች፣ "በተለይም እንግዶችን በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና በፍቅር ያስተናገዳችሁ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን፣ አባገዳዎችን፣ ሃደ ሲንቄዎችን፣ ፎሌዎችን፣ የጸጥታ አካላትን እና አመራሮቻችንን፣ በራሴ እና በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ አመሰግናለሁ" ብለዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: