Search

ኢሬቻ፦ የኅብረ-ብሔራዊነት ትርክት ማዕከል

ቅዳሜ መስከረም 23, 2019 130

የኢሬቻ በዓል የኢትዮጵያውያንን ጥንታዊ ባህላዊ እና ትውፊታዊ ብዝኃነት በደማቅ ሁኔታ ከሚያሳዩ ታላላቅ የአደባባይ መድረኮች አንዱ ነው።

በየዓመቱ በሆረ ፊንፊኔ እና በሆረ አርሰዲ በታላቅ ሥነ-ሥርዓት የሚከበረው ይህ የምሥጋና በዓል፣ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ዜጎች የሚገናኙበት፣ ማኅበራዊ ትሥሥራቸውን የሚያጠናክሩበት እና ኅብረ-ብሔራዊ ብዝኃነታቸውን የሚያደምቁበት የጋራ ሀብት ነው።

በዚህም ዘመናዊቷ ኢትዮጵያ በባለብዙ ማንነት ውበት ላይ የተመሠረተ የጋራ ትርክት እየገነባች መሆኗን በተግባር የሚያስመሰክር ታላቅ መድረክ ሆኗል።

በዩኔስኮ በማይዳሰስ የዓለም ባህል ቅርስነት የተመዘገበው የገዳ ሥርዓት አካል የሆነው ኢሬቻ፣ ዋቃ (ፈጣሪ) ለሰጠው ሰላም እና ጸጋ፣ ላለፈው የክረምት ወቅት እና ለተገኘው በረከት ምስጋና የሚቀርብበት እንዲሁም ለቀጣዩ ዘመን ብሩህ ተስፋ የሚሰነቅበት ደማቅ ሁነት ነው።

የክረምቱ ጎርፍ እና ጭጋግ አልፎ፣ ተፈጥሮ በዐደይ አበባ የምታጌጥበት የመፀው (ብራ) ወቅት ማብሰሪያ መሆኑ የችግር እና የጨለማ ማብቃትን፣ የብርሃን እና የተስፋ መምጣትን ያበሥራል።

ተሳታፊዎች የሰላም፣ የእርቅ እና የብልጽግና ተምሳሌት የሆነውን እርጥብ ሣር እና ዐደይ አበባ በእጃቸው ይዘው ወደ ወንዝ እና ሐይቅ ዳርቻዎች ሲያመሩ የሚታየው ትዕይንት የኢትዮጵያን ውብ አብሮነት ያጎላል።

ኢሬቻ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መቻቻልን በማጎልበት ረገድ የሚጫወተው ሚና የላቀ ነው። በበዓሉ ማዕከላዊ እሴት የሆነው "ነጋ" (ሰላም) ሐሳብ በገዳ ሥርዓት ውስጥ ያለውን የውይይት፣ የእርቅ እና የመግባባት ባህል የሚያንጸባርቅ ነው።

ይህም ለኢትዮጵያ የፖለቲካ እና ማኅበራዊ ምኅዳር እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የመከባበር እና የመቻቻል ሥነ-ልቦና ይገነባል።

የአባ ገዳዎች እና የሃደ ሲንቄዎች የምርቃት እና የእርቅ መልዕክቶች በልዩነቶች መካከል ድልድይ በመፍጠር ቅሬታዎችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ጥበብን ያስተምራሉ።

ከዚህም ባሻገር በዓሉ ዘላቂ የጋራ ትርክት ለመገንባት ጠንካራ መሠረት ይጥላል። ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ የልዩ ልዩ ብሔር ብሔረሰቦች ተወካዮች በባህላዊ አልባሳታቸው አጊጠው በበዓሉ ላይ በጋራ በመሳተፋቸው፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና ወንድማማችነት ይበልጥ ይጎለብታል።

ኢሬቻ የኦሮሞ ሕዝብ እሴት ከመሆን አልፎ የመላው ኢትዮጵያውያን የጋራ መገናኛ አደባባይ መሆኑ የሰላም፣ የዕድገት እና የአንድነት የጋራ ትርክት እንዲፈጠር ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።

ከባህላዊ እና ማኅበራዊ ፋይዳው በተጨማሪ በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኚዎችን በመሳብ ለቱሪዝም ዕድገት እና ለገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ይህ በዓል፣ በጠንካራ የጋራ ትርክት ላይ የተመሠረተች ብሩህ ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ጉዞ ውስጥ የማይተካ ታሪካዊ ድርሻ አለው።

በለሚ ታደሰ

#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: