Search

የልምላሜው እርጥብ ሳር፣ የይቅርታ እና የአብሮነት መገለጫው "ኢሬቻ"

ቅዳሜ መስከረም 23, 2019 120

የኢሬቻ በዓል በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በክረምት ወቅት ከመለያየትና ከመራራቅ በኋላ ሕዝቡን በአብሮነት ብርሃን ለማየት ያበቃውን ፈጣሪ (ዋቃ) የሚያመሰግንበት፣ የሰላምና የመልካም ምኞት መግለጫ የሆነ ታላቅ የበጋ መግቢያ በዓል ነው።

በዓሉ በሁለት መንገድ ይከበራል። የመጀመሪያው የክረምቱ ጭጋግ አልፎ ለፈካው ወራት ምስጋና የሚቀርብበት "ኢሬቻ መልካ" (በውኃ ዳርቻ) ሲሆን፤ ሁለተኛው የበጋው ወራት አልፎ የበልግ ዝናብና እርጥበት ሲጠበቅ "እርጥበት አትንፈገን" ተብሎ ፈጣሪ የሚለመንበት "ኢሬቻ ቱሉ" (በተራራ ላይ) ነው።

በዓሉ በዋናነት በአዲስ አበባ ሆረ ፊንፊኔ እና በቢሾፍቱ ሆረ ሀርሰዲ በከፍተኛ ደምቀት ይከበራል።

ከዚህ በዓል ጀርባ ያለው ማኅበራዊ እሴት እጅግ የጎላ ነው። ወንዞች በመሙላታቸው ምክንያት ተራርቆ የቆየው ሕዝብ ናፍቆቱን ለመወጣትና ዘመድ ለመጠየቅ ውብ ባህላዊ ልብሱን ለብሶ በሕብረት ያመራል።

በዚህ በዓል ፀብና ቂም ቦታ የላቸውም። "ሳል ይዞ ስርቆት፣ ቂም ይዞ ጸሎት" እንዲሉ፤ የተጣላ ታርቆና ቂሙን ረስቶ በንጹሕ ልቦና ወደ ውኃው አካል በመሄድ ፈጣሪውን ያመሰግናል።

በሥነ-ሥርዓቱ ወቅት በእጅ የሚያዘው እርጥብ ሳርና አበባ የልምላሜና የመልካም ምኞት ምልክት ነው። ሥነ-ሥርዓቱን ሃደ ሲንቄዎች እርጥብ ሳርና ጮጮ፣ አባ ገዳዎች ደግሞ ቦኩና አለንጌ ይዘው ሲመሩት፤ ወደ ውኃው በመቃረብ "ያ መሬሆ..." እያሉ ለፈጣሪ ምስጋና ያቀርባሉ።

በዓሉ በአባ መልካ ተከፍቶ በአባ ገዳዎች ከተመረቀ በኋላ፣ መላው ሕዝብ በአንድነት ያከብረዋል።

ኢሬቻ ከኦሮሞ ሕዝብ አልፎ የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች፣ የትውልደ ኢትዮጵያውያንና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ማዕከል ነው። ታዳሚዎች የየራሳቸውን ባህላዊ አልባሳት ለብሰው በቋንቋቸው ፈጣሪን ያመሰግኑበታል። ይህ በዓል እውነተኛ ወንድማማችነት የሚታይበትና አብሮነት የሚጠናከርበት ታላቅ ሀገራዊ እሴት ነው።

በተጨማሪም ባህላዊ አልባሳትንና ምግቦችን ከማስተዋወቁ በላይ ለገበያና ለኢኮ-ቱሪዝም ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው። ስለሆነም ይህንን የሰላም፣ የይቅርታና የምስጋና የጋራ እሴት ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ማስተላለፍ የሁላችንም ታሪካዊና ባህላዊ ኃላፊነት ነው።

በብሌን ደምበሎ

#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: