Search

"መሬዎ"፡- የበደል ንጻት፣ የሰላም መማጸኛ እና የአዲስ ዘመን ተስፋ

ቅዳሜ መስከረም 23, 2019 122

ኢትዮጵያውያን ለዘመናት በጋራ የመኖር ታሪካቸው ውስጥ አለመግባባቶችን የሚፈቱበት፣ ቁስሎችን የሚሽሩበት እና ሰላምን የሚያተርፉበት በርካታ ባህላዊ እና መንፈሳዊ የእርቅ መድረኮች አሏቸው።

ከእነዚህም መካከል ኢሬቻ አንዱ ሲሆን፣ በበዓሉ ወቅት በውኃ ዳርቻዎች እና በተራሮች ላይ የሚዜመው "መሬዎ" የመማጸኛ ሥነ-ሥርዓት ይጠቀሳል።

"መሬዎ" ማለት "ምሕረትህ በእኛ ላይ ይሁን፣ ማረን ወይም እዘንልን" ማለት ነው። ሕዝቡ አስቸጋሪውንና ጨለማውን የክረምት ወቅት አልፎ ለብርሃናማው አዲስ ዘመን ስላበቃው ፈጣሪውን የሚያመሰግንበት፣ ካለፈው ጭጋግ ወደ አዲስ ተስፋ የሚሸጋገርበት ታላቅ የይቅርታ ባህል ነው። ይህ እሴት በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ከጀመረችው ሀገራዊ የምክክር ሂደት ጋር ጥልቅ የታሪክ፣ የተስፋ እና የይቅርታ ትስስር አለው።

በኢሬቻ እሳቤ ክረምት አዝዕርት የሚያድጉበት የተስፋ ወቅት ቢሆንም፣ የውኃ ሙላትና የስጋት ጊዜ ጭምር ነው። ሀገራችንም ለዘመናት የቆዩ የታሪክ ትርክቶች እና የፖለቲካ አለመግባባቶችን አሳልፋለች።

የመሬዎ ጥሪ የክረምቱን ጭጋግ አሳልፎ ወደ ብርሃን መሸጋገርን እንደሚያስብ ሁሉ፣ ሀገራዊ ምክክሩም ኢትዮጵያን ከልዩነትና ከጥቅመኝነት ክረምት አውጥቶ ወደ ዘላቂ ሰላም የሚያሸጋግር ትልቅ መድረክ ነው።

መሬዎ ያለፈውን በደል በመካድ ሳይሆን፣ ጥፋትን አምኖ በመቀበልና ትህትናን በማሳየት የሚከናወን የምህረት ጥሪ ነው። ምክክሩም ጠመንጃ ያነሱና ልዩነት ያላቸው ወገኖች ቁስላቸውን ይዘው የቀረቡበት፣ አሸናፊና ተሸናፊ ሳይኖር በይቅርታ አብረው ለመኖር መንገድ የከፈተ ዕድል ነበር።

በሥነ-ሥርዓቱ ማጠናቀቂያ አባ ገዳዎችና የቃሉ መሪዎች ውኃውን በመቅዳት እርጥብ ሳሩን ነክረው በሕዝቡ ላይ ይረጫሉ። ውኃ ያጥባል፤ እርጥብ ሳር ደግሞ ልምላሜንና ሰላምን ይወክላል። ሀገራዊ ምክክሩም የመታደሻ ወንዝ በመሆን የጥላቻና የቂም በቀል አስተሳሰቦችን በውይይት አጥቦ፣ በምትኩ የታጨደውን የሰላም እርጥብ ሳር በመላው ሀገራችን ላይ የሚረጭበት መድረክ ነው።

መሬዎ ኢትዮጵያውያን ከዘመናዊ የፖለቲካ አስተሳሰቦች በፊት የነበራቸውን ጥልቅ ሀገር በቀል የእርቅ ሥርዓት ያሳያል። በሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ የተደረገው ጥረትም እነዚህን የህዝቡን ባህላዊ፣ መንፈሳዊ እና ማህበራዊ የእርቅ እሴቶች መነሻ በማድረግ በዘመናዊ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ነው።

መሬዎ የቃል ብቻ ሳይሆን የልብ ስብራት ማጠቢያ ሀብታችን እንደመሆኑ፣ በምክክሩ አማካኝነት ለሁሉም የሚሆን አዲስ ምዕራፍ እንጀምራለን።

በሃና ምንዳሁን

#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: