Search

ኢሬቻ፦ የኦሮሞ ሕዝብ ፈጣሪው ላደረገለት መልካም ነገር ሁሉ ምስጋናውን የሚያቀርብበት ታላቅ መድረክ

ቅዳሜ መስከረም 23, 2019 115

የገዳ ሥርዓት ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ምሰሶዎች መካከል በዋናነት የሚጠቀሰው የኢሬቻ በዓል ነው።

ኢሬቻ፣ ከሰው ልጅ የፈጣሪ አምልኮ መጀመር ጋር አብሮ የዘለቀ፣ በኩሽቲክ ባህል እና ማኅበራዊ ሕይወት ውስጥ የጠለቀ ሥር ያለው የምስጋና፣ የሰላም እና የእርቅ በዓል እንደሆነ ይገለጻል።

የኦሮሞ ሕዝብ የዓለም ፈጣሪ (“ዋቃ”) ላበረከተለት መልካም ነገር ሁሉ ጮቆርሳ (እርጥብ ሣር) ይዞ ምስጋናውን የሚያቀርበው በኢሬቻ ሥርዓት ነው።

የሕዝቡ ታሪክ እና ባህል ውስጥም ኢሬቻ የሚለው ቃል በራሱ እርጥብ ሣርን ወይም አበቦችን የሚወክል ሲሆን፣ እርጥብ ሣር ደግሞ የሕይወት፣ የለምለምነት፣ የሰላም እና የብልጽግና ተምሳሌት ሆኖ ያገለግላል።

በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ እርጥብ ሣር ለፈጣሪ የሚቀርብ የምስጋና ገጸ-በረከት ብቻ ሳይሆን፣ ለማኅበራዊ እሴቶችም ታላቅ መገለጫ ነው። ለጋብቻ ጥያቄ፣ ለታላላቅ መልዕክቶች እንዲሁም በፈጣሪ ስም ለሚደረጉ ቃለ-መሐላዎች ሁሉ እርጥብ ሣር መያዝ የዘለቀ ባህል ነው።

በገዳ ሥርዓት ማዕቀፍ ውስጥ ኢሬቻ በ‘ዋቄፈና’ /Waaqeffannaa (ፈጣሪን ማምለክ)/ ላይ የተመሠረተ ሆኖ ሁለት ዋና ዋና ታላላቅ ምዕራፎች አሉት።

አንደኛው ኢሬቻ መልካ (የውኃ ዳር /የብራ ኢሬቻ/) ነው

ክረምቱ አብቅቶ ብራ (የመፀው) ወራት ሲጠባ የሚከበር ታላቅ የምስጋና በዓል ነው። ክረምት በኦሮሞ ፍልስፍና ጥልቅ ምሥል አለው፤ ክረምት የጨለማ እና የእስራት ምሳሌ ነው። ጭቃው፣ ረግረጉ፣ ጎርፉ እና ኃይለኛው ዝናብ ሰዎችን ያራርቃል፣ ወንዞችን ያሞላል።

መስከረም ሲጠባ ግን ብርሃን ይወጣል፤ ወንዞች ይጎድላሉ፣ ረግረጉ ይደርቃል፣ ምድሪቱ በለምለም አበቦች ታበብራለች። የኦሮሞ ሕዝብም ከዚህ የጨለማ ወራት ወደ ብርሃን፣ ከስጋት ወደ ሰላም ላሸጋገረው ዋቃ (ፈጣሪ) ምስጋና ለማቅረብ ወደ ውኃ አካላት (ሆራ እና መልካ) ይሄዳል። ውኃ ለሕይወት ሁሉ መሠረት በመሆኑ፣ ለፈጣሪ ምስጋና ማቅረቢያ ታላቅ ስፍራ ሆኖ ያገለግላል።

ሁለተኛው ደግሞ ኢሬቻ ቱሉ (የተራራ ኢሬቻ) ነው

በበጋው ወቅት ፀሐይ እና ሀሩር በሚበረታበት፣ ምድሪቱ በድርቅ በምትቃጠልበት ጊዜ የሚካሄድ የጸሎት እና የልመና ሥነ-ሥርዓት ነው። ሕዝቡ ወደ ቱሉ (ተራራ) በመውጣት ፈጣሪ ለፍጡራኑ አዝኖ ደመናን አቅዝቅዞ ዝናብ እንዲያዝንብ፣ ከብቶችን ከለምለም ሣር እንዲያገናኝ፣ ጎርፍ እና መቅሰፍትን እንዲከለክል በጸሎት ይማጸናል።

ቱሉ (ተራራ) ለሰማይ ቅርብ እንደመሆኑ ፈጣሪ ጸሎትን ፈጥኖ ይሰማል የሚል መንፈሳዊ እምነት ይንጸባረቅበታል።

በተጨማሪም መንገደኞች ወንዝ ባገኙ ቁጥር በእርጥብ ሣር ከውኃው እየነከሩ ለፈጣሪ የሚያቀርቡት የግል ኢሬቻ የዕለት ተዕለት የምስጋና መግለጫ ነው።

ኢሬቻ የሃይማኖታዊ ምስጋና መድረክ ብቻ ሳይሆን የጠነከረ ማኅበራዊ መስተጋብር እና የእርቅ መድረክ ነው። “ቂም ይዞ ጸሎት አይቻለም” በሚለው የገዳ ሕግ መሠረት፣ ወደ ኢሬቻ ስፍራ የሚሄድ ማንኛውም ሰው ቀደም ብሎ ከጎረቤቱ፣ ከወዳጁ እና ከተጣላው ሰው ጋር ታርቆ፣ ልቡን ከቂም በቀል አጽድቶ መቅረብ አለበት። ኢሬቻ የልብ እና የቀልብ መንጻት ቦታ ነው።

በዚህ ታላቅ በዓል ላይ የሴቶች (ሃዳ ሲንቄዎች) ሚና እጅግ የጎላ እና የገዳ ሥርዓትን የእኩልነት እሴት የሚያሳይ ነው። ወደ መልካ በሚደረገው ጉዞ አባ ገዳዎችን እና ማኅበረሰቡን መርተው ከፊት የሚጓዙት እርጥብ ሣር በእጃቸው የያዙት ሃዳ ሲንቄዎች ናቸው።

“መሬዎ… መሬዎ” እያሉ ፈጣሪን የሚያመሰግኑት እና ሰላምን፣ ፍቅርን፣ ብልፅግናን እና አንድነትን የሚያውጁት እነዚሁ እናቶች ናቸው።

የኢሬቻ በዓል ከ16ኛው ክፍለ ዘመን በኋላ የተከናወኑ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ለውጦችን (የክርስትና እና የእስልምና ሃይማኖቶች መስፋፋትን) ተከትሎ የቀደመ ገጽታው እየተቀዛቀዘ መጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ የጽናትና የማንነት መገለጫ በመሆኑ ሙሉ በሙሉ ሳይጠፋ ለዘመናት ዘልቋል።

በአሁኑ ወቅት ኢሬቻ ታሪካዊ እና ባህላዊ ሕዳሴውን አግኝቶ፣ በዩኔስኮ ከተመዘገበው የገዳ ሥርዓት ጋር ተያይዞ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ እሴት ሆኗል። ኢሬቻ መልካ በየዓመቱ ከመስቀል በዓል በኋላ በሚመጣው እሑድ በሆረ ፊንፊኔ እና በሆረ አርሰዴ ሚሊዮኖች ታድመውበት በደመቀ ሁኔታ ይከበራል።

ኢሬቻ የሰው ልጅ ከፈጣሪው፣ ከተፈጥሮ እና ከባልንጀራው ጋር የሚያደርገው ታላቅ የሰላም፣ የፍቅር፣ የእርቅና የምስጋና ቃል-ኪዳን ሕያው መገለጫ ነው።

በዮናስ በድሉ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: