Search

በአዲስ መንፈስ፣ አዲስ ውል፦ አዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታ

ሰኞ መስከረም 25, 2019 305

አዲሱ የመደመር መንግሥት ምሥረታ ኢትዮጵያ ሀገረ መንግሥት ግንባታዋን በጽኑ መሠረት ላይ ለማቆም የምታደርገው የሽግግር ምዕራፍ ነው። ይህ አዲሱ የመደመር መንግሥት ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ለማሻገር ሦስት መሠረታዊ ማዕዘኖችን አጣምሮ መጓዝ እንደሚጠበቅበትም ይገለጻል።

የመጀመሪያው ምሰሶ ምናባዊ ራዕይን ወደ ተጨባጭ የማድረግ አቅም የመለወጥ ብቃት ነው። መልካም እሳቤዎች እና ንግግሮች ብቻቸውን ሀገርን እንደማይቀይሩ ግልጽ ነው።

አዲሱ የመደመር መንግሥት እንደ አዲስ አበባ የኮሪደር ልማት ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ ከዕቅድ ወደ መሬት ያወረደበትን የፈጻሚነት አቅም በሁሉም ዘርፍ እንዲደግመው ይጠበቃል።

ማሰብ እና መናገር ብቻ ሳይሆን ተግባር ላይ ያልተፈተሸ እሳቤ ዋጋ እንደሌለው በመገንዘብ፣ የመደመር መንግሥት የጀመራቸውን ትልሞች ዳር በማድረስ የመጨረስ ልህቀትን በተቋም ደረጃ ሊያሠርጽ ይገባል። ፍላጎትን ከግለሰብ አልፎ ወደ ማኅበረሰብ በማሸጋገር ተቋማዊ የማድረግ ጅማሮዎች የአዲሱ የመደመር መንግሥት የዕለት ተዕለት መገለጫዎች መሆን አለባቸው።

ሁለተኛው ምሰሶ ከአዲሱ የመደመር መንግሥት የሚጠበቀው ትልቅ ጉዳይ ተላማጅነት እና ተለዋዋጭነትን የተላበሰ መሆን ነው። ኋላ ቀር የሆነውን የኢኮኖሚ መዋቅር ወደ ዘመናዊ አምራችነት ለመለወጥ፣ ጊዜውን እና ሁኔታውን ያገናዘበ ገቢር ነበብ (ፕራግማቲክ) አካሄድ መከተልን ይጠይቃል።

በትንሽ ኩሬ ውስጥ ከመወሰን፣ አጥርን ጥሶ መውጣት እና ውድቀትን ሳይፈሩ ከባድ ውሳኔዎችን ማሳለፍ የግድ ይላል። የመደመር መንግሥት በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚያጋጥሙትን ተግዳሮቶች ለመፍታት የዕውቀት፣ የጊዜ እና የቦታ አጥሮችን በምናባዊ ከፍታ በመስበር፣ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያሉ ተራማጅ ውሳኔዎች መውሰድ ይጠበቅበታል።

የችግሮቹን ስፋት እና ውስብስብነት ተረድቶ በፍጥነት መፍትሔ የሚያመነጭ፣ እርካታን ተጽይፎ ሁልጊዜም ከተደረሰበት ተሻግሮ የሚያይ ተለዋዋጭ አቅም መፍጠር የሕልውና ጉዳይ ነው።

የመጨረሻው ደግሞ አዲሱ የመደመር መንግሥት የሚያስተዋውቀው አዲሱ ማኅበራዊ ውል ከሦስት ታሪካዊ ኃላፊነቶች ጋር የተቆራኘ ነው።

ይኸውም የነበረውን ጠብቆ ማቆየት፣ የተበላሸውን ማረም እና የጎደለውን ማሟላት ነው። ሕዝቡ ከዚህ የመደመር መንግሥት የሚጠብቀው ቀደምት ትውልዶች ያቆዩልንን የነፃነት፣ የአብሮነት እና የሀገር ፍቅር እሴቶችን ሳይሸራረፉ ማስቀጠልን ነው።

በተጓዳኝም በሂደት የተፈጠሩ ስህተቶችን፣ ታሪካዊ ቁስሎችን እና ፖለቲካዊ ስብራቶችን በእውነተኛ ሀገራዊ መግባባት መንፈስ እንዲያክም በጽኑ ይፈለጋል። ይህ ማኅበራዊ ውል የተሟላ የሚሆነው መንግሥት ያለፈውን ከማረም ባለፈ ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገር ዘመናዊ፣ አካታች እና ጠንካራ የፖለቲካ እንዲሁም የኢኮኖሚ ሥርዓት ሲገነባ ነው።

በአጠቃላይ አዲሱ የመደመር መንግሥት የብልጽግና ጉዞውን ዳር ለማድረስ ራዕይን የመፈጸም አቅም፣ በፈተናዎች የማይበገር ተላማጅነት እንዲሁም ትውልድ አሻጋሪ የሆነውን የሦስትዮሽ ማኅበራዊ ውል በተግባር በማሳየት የጸናች ሀገረ መንግሥት የመገንባት ታሪካዊ አደራውን መወጣት ይጠበቅበታል።

በበረከት ሽመልስ

#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: