Search

የመደመር መንግሥት ምሥረታ በኢትዮጵያ

ሰኞ መስከረም 25, 2019 160

የዓለማችንን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ታሪክ ስንመረምር፣ አውሮፓውያን የአብርሆት ዘመን የፈጠሩት የሐሳብ አብዮት የዓለምን የታሪክ አቅጣጫ የቀየረ ክስተት ሆኖ እናገኘዋለን።

የኢንዱስትሪ አብዮትን ተከትሎ የተወለደው የካፒታሊዝም አስተምህሮ አዳዲስ የሀብት ፈጠራ መንገዶችን አስተዋወቀ። ይህ የካፒታሊዝም ርዕዮት ከጊዜ በኋላ እያደገ እና እየዳበረ መጥቶ ወደ ሊበራሊዝም ተሸጋገረ። ሊበራሊዝም ሁሉንም ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብር ገበያ መር በሆነ መንገድ ለመምራት የሚጥር ሲሆን፣ ዋነኛ ማጠንጠኛው ደግሞ የግለሰብ መብት እና ነፃነት ነው።

ዛሬ ላይ የምዕራባውያኑ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የኢኮኖሚ መዋቅር፣ ሃይማኖታዊ እና ማኅበራዊ ሕይወታቸው፣ አልፎ ተርፎም የትምህርት ሥርዓታቸው ሙሉ በሙሉ በሊበራሊዝም እሳቤ የተቃኘ ነው። ይህ ሥርዓት ለእነሱ በሚገባ የሠራው እና ሀገሮቻቸውን የገነባው፣ ከራሳቸው ታሪክ፣ የባሕል ዝግመተ ለውጥ እና ተሞክሮ አያይዘው ስላመነጩት ነው።

ይሁን እንጂ፣ ይህንን የምዕራባውያን ርዕዮተ ዓለም እንደወረደ በመቅዳት ወደ ራሳቸው ሀገር አውድ ለማምጣት የሞከሩ በርካታ ሀገራት ክፉኛ ፈራርሰዋል፤ ጥልቅ ምስቅልቅል ውስጥም ገብተዋል። በላቲን አሜሪካ እና በተለያዩ የአፍሪካ ክፍሎች የሚገኙ በርካታ ሀገራት የራሳቸውን ሀገር በቀል ዕውቀት፣ ማኅበራዊ እሴት እና ታሪካዊ ዳራ ወደ ጎን በመተው የሊበራሊዝምን እሳቤ በግዴታ ለመጫን ባደረጉት ሙከራ ከባድ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ቀውሶችን አስተናግደዋል።

እነዚህ ሀገራት ከራሳቸው ዕውቀት፣ ከራሳቸው የሕዝብ ግንዛቤ፣ እንዲሁም ከራሳቸው ባሕልና ታሪክ የተቀዳ ፍልስፍናን በመጠቀም የፖለቲካ ሥርዓታቸውን ለመምራት ጥረት ባለማድረጋቸው ምክንያት የመንግሥት መፍረስ እና ማኅበራዊ መበታተን ዕጣ ፈንታቸው ሆኗል።

የኢትዮጵያ የመደመር መንግሥት ምሥረታ ከዚህ የውድቀት ታሪክ እና የቅጂ ፖለቲካ የተለየ፣ መሠረታዊ እና ታሪካዊ ለውጥ ያመጣ ጽንሰ ሐሳብ ነው። መደመር በድንገት ከባዶ የተፈጠረ ጽንሰ ሐሳብ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያን ታሪካዊ እውነት፣ ነባራዊ ሁኔታ፣ እንዲሁም እንደ ገዳ፣ ሽምግልና እና ደቦ ያሉ የዘመናት አብሮ የመኖር እሴቶችን በሚገባ ከመመርመርና ኢትዮጵያን በጥልቀት ከማወቅ የመነጨ ጥልቅ እሳቤ ነው። ይህ ፍልስፍና ሀገር በቀል ዕውቀትን እና ማኅበራዊ እሴትን ከዓለም አቀፋዊ የሳይንስ ዕውቀት ጋር በማዋሃድ፣ ሀገራችን ያላትን ግዙፍ እምቅ አቅም ወደ ተጨባጭ ተግባር የሚቀይርበትን ብሩህ መንገድ በግልጽ ያሳያል።

በዚህ የፍልስፍና ማዕቀፍ ላይ የቆመው የመደመር መንግሥት ባሕሪ እና መገለጫ ከተለመዱት የፖለቲካ ሥርዓቶች እጅግ የተለየና የላቀ ሆኖ እናገኘዋለን። የመደመር መንግሥት ኢኮኖሚውንም ሆነ ፖለቲካውን ሙሉ በሙሉ ራሱ ጠቅልሎ በመያዝ የዜጎችን የፈጠራ ተነሣሽነት ከሚያፍነው አዛዥና ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት፣ እንዲሁም ሁሉንም ነገር ለገበያ ጥሎ ከልማት ኃላፊነቱ ከሚያፈገፍገው የሊበራሊዝም ጫፍ ወጥቶ የወጣ መንግሥት ነው። ይህ ሥርዓት የግሉን ዘርፍ አይተካም፤ ይልቁንም አምራችነትን ያፋጥናል፣ ምቹ የኢንቨስትመንት አውድን ይፈጥራል፣ እንዲሁም የሀገር ውስጥ እሴትን ያስቀራል፡፡

መደመር ከሌሎች ከውጭ ከተቀዱ ርዕዮተ ዓለማት የሚለየው አንደኛ ገቢር ነበብ (ፕራግማቲክ) በመሆኑ ነው። በአንድ ርዕዮተ ዓለማዊ ዶግማ ታስሮ ከመቅረት ይልቅ፣ በጊዜውና በሁኔታው ራሱን እያደሰ አዳዲስ የመፍትሔ ሐሳቦችን ያመነጫል። ሁለተኛው ልዩነቱ ወርቃማ አማካይ መከተሉ ነው። ሌሎች ርዕዮተ ዓለሞች ማኅበረሰብን በጠላትና በወዳጅ ጎራ ሲከፍሉ፣ መደመር ግን ጽንፎችን በማስታረቅ የጋራ መግባባት ላይ ያተኩራል።

በተጨማሪም፣ መደመር የግለሰብን መብት የሚያቀነቅነውን የሲቪክ ብሔርተኝነትን እና የቡድን መብት ላይ የሚያጠነጥነውን የማኅበረሰብ ብሔርተኝነትን ሳያበላልጥ በእኩል ሚዛን የሚያስተናግድ አዲስ ሥርዓት ይዘረጋል። አብዛኞቹ ርዕዮተ ዓለሞች አንዱን ፍላጎት ለማሟላት ሌላውን ሲደፈጥጡ፣ መደመር የሰውን ልጅ ሁለንተናዊ ፍላጎት በእኩልነት ይመለከታል።

እንዲሁም፣ የትናንት ታሪክን ሙሉ በሙሉ አፍርሶ ከዜሮ የመጀመር አባዜን አጥብቆ ይቃወማል። ይልቁንም ካለፉት ዘመናት የወረስነውን "ወረት" ጠብቆ በማስፋትና ስህተቶችን በማረም የትውልድ ቅብብሎሽን ያረጋግጣል። በአጠቃላይ፣ መደመር እና የመደመር መንግሥት የዜሮ ድምር ፖለቲካን ትተው፣ ትብብርንና ወንድማማችነትን መሠረት በማድረግ ኢትዮጵያን ወደማይቀለበስ የብልጽግና እና የሥልጣኔ ከፍታ የሚያሸጋግሩ ዘመናዊ የሀገር ግንባታ ጥበቦች ናቸው።

ባለፉት ሰባት እና ስምንት ዓመታት፣ በኢትዮጵያ የመደመር መንግሥት ወደ ሥልጣን በመምጣት ይህንን እሳቤ በተግባር ሲፈትነው እና ተግባራዊ ሲያደርገው ቆይቷል። በዚህ ጊዜ ውስጥ የተበታተነ አቅምን በመሰብሰብ ኢትዮጵያን ከመሠረቱ ትራንስፎርም የሚያደርጉ ሥር ነቀል እና መሠረታዊ ለውጦች ተካሂደዋል። ከመሠረተ ልማት ዝርጋታ እስከ ማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም፤ ከተቋማዊ ግንባታ እስከ ዲጂታል ሉዓላዊነት እና የዜጎች ክብርን ወደሚያስቀድም አገልግሎት የተደረጉት ጉዞዎች የመደመር ፍልስፍና በተግባር ያመጣቸው ፍሬዎች ናቸው። የቆዩ ማኅበራዊ ቁስሎችን ለማከም የተጀመሩ የብሔራዊ እርቅ ሥራዎች፣ እንዲሁም ፖለቲካን ከጥላቻ አውጥቶ በሐሳብ ልዕልና ላይ ለመመስረት የተደረጉት ጥረቶች የዚሁ የመደመር መንግሥት ስኬቶች ናቸው።

እነዚህን ሥር ነቀል ለውጦች ተከትሎ፣ እነሆ ዛሬ የመደመር መንግሥት በኢትዮጵያ 7ኛው ዙር አጠቃላይ ምርጫ በሕዝቡ ጠንካራ ይሁንታ በማግኘት፣ ለሁለተኛ የምርጫ ዘመን ሀገራችንን ወደ ፊት የመምራት ግስጋሴውን ለማስቀጠል ታሪካዊ ዕድሉን አግኝቷል።

የመደመር መንግሥት፣ የኢትዮጵያውያን መልክ ነው። ከራሱ ከኢትዮጵያዊ ልጆች የፈለቀ፣ ከኢትዮጵያዊ አእምሮ እና ነባራዊ እውነት የተቀዳ የሐሳብ ልዕልና ነው። የውጭ ርዕዮተ ዓለሞችን እንደወረደ በመቅዳት ሳይሆን፣ የራሳችንን ታሪክ፣ ጸጋ፣ ዕውቀት እና አቅም አሰባስበን፣ ችግሮችን የሚቋቋም፣ ዜጎች በነፃነት እና በብልጽግና የሚኖሩባት፣ ዘላቂ የሆነች የኢትዮጵያ ሥልጣኔን ለመገንባት መደመር ብቸኛው እና አስተማማኙ መንገድ ሆኖ ይቀጥላል። ይህ ምርጫም የዚህ ሀገር በቀል ጽንሰ ሐሳብ ሌላኛው የታሪክ ምዕራፍ ማረጋገጫ ነው።

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: