ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግብፅ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የምታደርገው የተጣደፈ የፖለቲካ እና ዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴ፣ የራሷን የውስጥ ጥቅም ከማስጠበቅ ይልቅ የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የልማት ግስጋሴ እንቅልፍ እንደነሳት በግልጽ የሚያሳይ ሁነኛ ማሳያ ሆኗል።
በግብፅ የባሕር ዳርቻ ከተማ ኒው አል-ዓላሜይን የግብፅ ፕሬዝዳንት አብደል ፈታህ አል-ሲሲ የኤርትራ፣ የሶማሊያ እና የሱዳን መሪዎችን በመሰብሰብ ያደረጉት ምክክር የዚሁ እኩይ አካሄድ ማሳያ ነው።
ይህ ስብስብ በውጭ ገጽታው የቀጣናዊ ደኅንነት እና የጋራ ትብብር መድረክ አስመስሎ ለመቅረብ ቢሞክርም ዋነኛ ስውር አጀንዳው ግን በአፍሪካ ቀንድ ያለውን የፖለቲካ ምኅዳር ማበላሸት እና በኢትዮጵያ ላይ ጂኦፖለቲካዊ እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመፍጠር ያለመ እንደሆነ የቀጠናው ተጨባጭ ሁኔታ ያረጋግጣል።
ይሁን እንጂ ይህ ጥረት መሬት ላይ ካለው ነባራዊ እውነታ ጋር ፈጽሞ የተቃረነ በመሆኑ ከጅምሩ መና መቅረቱ አይቀሬ ነው።
ግብፅ ከኢትዮጵያ አንጻር ለዘመናት ስትከተለው የቆየችው የዜሮ ድምር የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ፣ ጎረቤቶችን በማነሳሳት እና የቀጣናውን ሰላም በማናጋት የተፈጥሮ ሀብትን በብቸኝነት የመቆጣጠር ስትራቴጂ ላይ የተመሰረተ ነበር።
የአሁኑ የካይሮ እንቅስቃሴ ግን ከቀደሙት ጊዜያት የሚለየው ከከፍተኛ ጭንቀት እና የመደናገጥ ስሜት የመነጨ መሆኑ ነው።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የውኃ ሕጎችን የጠበቀ ፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀምን መሠረት አድርጋ የመልማት አቋሟን በተግባር ማረጋገጧ እንዲሁም ተፈጥሮአዊ እና ሕጋዊ የቀይ ባሕር ጥያቄዋን ማጠናከሯ ካይሮን በእጅጉ አስደንግጧታል።
የኢትዮጵያ ጽኑ አቋም ግብፅ ለዘመናት የተመካችባቸውን እና ሌሎችን ያገለሉትን የ1929 እና የ1959 የቅኝ ግዛት ውሎች ተግባራዊነት የሌላቸው የታሪክ ማህደር ሰነዶች አድርጓቸዋል።
የካይሮው ስብስብ በይፋ ባወጣው መግለጫ በቀይ ባሕር አስተዳደር እና ደኅንነት ላይ የቀይ ባሕር ዳርቻ ሀገራት ብቻ ባለቤት ይሆናሉ ሲል የተለመደውን አግላይ ወሰን አስቀምጧል።
በተመሳሳይ አንደበት ደግሞ በዓባይ ወንዝ ላይ የሚከናወኑ ማንኛቸውም ፕሮጀክቶች የታችኞቹን ተፋሰስ ሀገራት ፈቃድ ማግኘት አለባቸው በማለት የኢትዮጵያን የተፈጥሮ ሀብት የመጠቀም ሉዓላዊ መብት ለመገደብ ይሞክራል።
ይህ አካሄድ የግብፅን ከፍተኛ የራስ ወዳድነት እና ፖለቲካዊ ግብዝነት እርቃኑን የሚያስቀር ነው። "ቀይ ባሕር ኢትዮጵያን አይመለከታትም፤ ዓባይ ግን የጋራችን ነው" የሚለው የካይሮ የተዛባ ትርክት፣ ከድንበሯ በሺዎች ኪሎ ሜትሮች ርቆ ከኢትዮጵያ ደጅ የሚፈልቀውን የዓባይ ወንዝ በባለቤትነት ለመቆጣጠር ከምታደርገው ከንቱ ድካም ጋር ሲነጻጸር አስገራሚ የሞራል ውድቀት ነው።
በአንጻሩ በጂኦግራፊ፣ በታሪክ እና በሕዝብ ትስስር ከቀይ ባሕር ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያላትን ኢትዮጵያን ከባሕር በር ለማግለል የምታሰላው ስሌት የቀጣናውን ተፈጥሯዊ ሚዛን የሚክድ ነው።
ይህ ዓይነቱ የቀዝቃዛው ጦርነት ዘመን የከበባ ዲፕሎማሲ በ21ኛው ክፍለ ዘመን የአፍሪካ ቀንድ ጨርሶ ቦታ የለውም። ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላትን፣ የአፍሪካ የፖለቲካ መዲና የሆነችውን እና የቀጣናው ዋና የኢኮኖሚ እንዲሁም የደኅንነት ምሰሶ የሆነችውን ኢትዮጵያን በጎረቤቶቿ በኩል ለመዝጋት መሞከር ዘመን ያለፈበት የታሪክ ስህተት ነው።
ግብፅ በሶማሊያ ወታደራዊ ኃይል ለማስፈር እና በአካባቢው ወታደራዊ ጣቢያዎችን ለመጠቀም የምታደርገው እንቅስቃሴ የቀጣናውን ሰላም የሚያረጋግጥ ሳይሆን፣ የምሥራቅ አፍሪካን ደኅንነት ይበልጥ አደጋ ውስጥ የሚከትት አደገኛ የጥፋት እርምጃ ነው።
የአፍሪካ ቀንድ ሀገራትን ዘላቂ ጥቅም የሚያረጋግጠው በካይሮ የተንኮል መረብ ውስጥ በመግባት ኢትዮጵያን ለማግለል በሚደረግ የጥፋት አጀንዳ ሳይሆን፣ በጋራ ልማት፣ በፍትሐዊ የሀብት አጠቃቀም እና በሁለገብ ትብብር ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ የባሕር በር የማግኘት ሰላማዊ እና ሕጋዊ ፍላጎትም ሆነ የዓባይን ውኃ ለልማት የመጠቀም ተፈጥሮአዊ መብት በሴራ ስብሰባዎች እና ጊዜ ባለፈበት የከበባ ስትራቴጂ የሚገታ አይደለም።
ኢትዮጵያ ጥቅሟን ለማስከበር ከምንጊዜውም በላይ በቂ ዝግጁነት፣ የማይናወጥ ጥንካሬ እና የማድረግ ብቃት አላት። በልማት ጉዞዋ ማንንም የማግለል፣ የሌሎችን ጥቅም የመንካት ወይም ዓለም አቀፍ ሕግን የመጣስ ፍላጎት የላትም።
ይሁን እንጂ የጋራ ተጠቃሚነት መርሕን ጠብቃ የምታደርገውን የከፍታ ጉዞ ለማደናቀፍ የሚሞክሩ የውስጥ እና የውጭ ኃይሎችን እኩይ ዓላማ የማክሸፍ ሙሉ አቅም ገንብታለች።
#ትልቅ_ሀገር #ትልቅ_ሕዝብ #ታላቅ_ርዕይ ሰንቃ የተነሳችው ኢትዮጵያ፣ በኒው አል-ዓላሜይን የተተበተበው ሴራ ከወረቀት እና ከሚዲያ ፍጆታ ባለፈ የቀጣናውን እውነተኛ የተፈጥሮ፣ የኢኮኖሚ እና የሕዝቦች ቁርኝት እንደማይለውጠው በተግባር እያረጋገጠች ትጓዛለች።
በለሚ ታደሰ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: