Search

የመደመር መንግሥት እየመጣ ነው!

ሰኞ መስከረም 25, 2019 251

ታሪክ በአጋጣሚዎች ድንኳን ሥር ብቻ አይጠለልም፤ የዘመናት የታፈነ ቁጭት፣ የሕዝብ ብርቱ መሻት እና የዕጣ ፈንታ ጥሪ ተጋጥመው በሚወልዱት ታላቅ የታሪክ እጥፋት ውስጥ እንጂ።

ኢትዮጵያ በነጠላ ፖለቲካዊ ትርክቶች ታንቃ፣ በኢኮኖሚ ውድቀት አፋፍ ተንገዳግዳ፣ በውጭ ዕዳ ቀንበር ጀርባዋ ጎብጦ በቆመችበት አፋፍ ላይ፣ ያ የታሪክ እጥፋት በመደመር መንግሥት ምሪት ታወጀ።

ያ ታሪካዊ ክስተት ሀገራዊ ሕልውናን ከዘመናዊ ሥልጣኔ ጋር አቆራኝቶ፣ የሕዝብን ሥነ ልቦናዊ ስብራት የመጠገን እና ኢትዮጵያን ካቀረቀረችበት ቀና የማድረግ ጽኑ ጉዞ ማስጀመሪያ ነበረ።

ይህን ታሪካዊ ጉዞ ያስጀመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ ያመለጡትን እና ያጣቸውን ዕድሎች ቁጭ ብሎ በመቁጠር የሚቆዝሙ ሳይሆኑ፣ ያለፈውን ወረት ጠብቆ የታዩ ስህተቶችን በዕውቀት እያረሙ ወደፊት በመገስገስ የሚያምኑ ተራማጅ እና የገቢር ነበብነት ጥበብ የተላበሱ ናቸው።

በቃላት ድርደራ ያልታጠረ፣ በተግባር ሜዳ የተፈተነ ብርቱ ጽናት። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ ከተለመደው የፖለቲካ ንግግር ባሻገር፣ ኢትዮጵያ በውስጧ የታመቀውን ሀብቷን አውቃ፣ ጥሪቷን ተረድታ እና ጸጋዎቿን ገልጣ እንድትታይ ያልፈነቀሉት ድንጋይ የለም።

ከጉባ በረሃ እስከ ቤኒሻንጉል ማማዎች፣ ከኦሞ ሸለቆ እስከ ደቡብ የተፈጥሮ ጸጋዎች ድረስ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ የተመላለሱበት አሻራ መሬት ላይ ጉልህ ምስክር ሆኖ ቆሟል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተራራ ሸለቆው፣ በጓዳ ጎድጓዱ፣ በፀሐይ እና በቁሩ እየተንከራተቱ የደከሙት ለአንዲት እናት ሀገር ክብር ነበር። የኢትዮጵያን አፈር እና ድንጋይ፣ ወንዝ እና ሸለቆ በማንበብ፣ የታመቁ የተፈጥሮ ሀብቶቿን ወደ ተጨባጭ ልማት የመቀየር ተዓምር ተከናወነ።

ሀገራችን ለዘመናት የተሸከመችውን የረሃብና የልመና ማቅ ለመግፈፍ የተካሄደው ተጋድሎ የምግብ ሉዓላዊነትን ዕውን አድርጓል። ልመናን የምትጸየፍ፣ በራሷ አፈር እና ላብ የምትተማመን ሀገር ዕውን ለማድረግ ባላቸው ጽኑ ራዕይ፣ የተረጂነትን የሥነ ልቦና ሰንሰለት በመበጠስ፣ ስንዴን ከውጭ ከማስገባት ወጥታ በአፍሪካ ቀዳሚ አምራች እና ላኪ እንድትሆን የተደረገበት መንገድ አርቆ አሳቢነታቸውን እና የሕዝብ አስተባባሪነትን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። የሌማት ትሩፋት ንቅናቄ እና በክረምት እና በበጋ የሚካሄደው የኩታ ገጠም እርሻ፣ ኢትዮጵያ በራሷ ላብ ቆማ የምትበላ ሀገር እንድትሆን አስችለዋታል።

የሰው ልጅን ከተፈጥሮ ጋር ያለውን ጥልቅ ግንኙነት እና የተፈጥሮን ሚዛን የጠበቀው የመደመር ፍልስፍና የሰውን አቅም ማጎልበት ብቻ ሳይሆን የተፈጥሮን እምቅ ኃይል ከሰው ልጅ ሕልውና ጋር በማስተሳሰር ለብቸኝነት እና ለስብራት ሁነኛ ምላሽ ሰጥቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን የተፈጥሮ እሳቤ በጠራ ፍልስፍናዊ መሠረት በማዋሃድ በዓለም ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ አኳኋን የመሩት የአረንጓዴ አሻራ ንቅናቄ፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት ብቻ ኢትዮጵያ በአስደናቂ ፍጥነት ወደፊት እንድትራመድ አድርጓታል።

ሀገራችን እስካሁን ባለው ጉዞ ከ56 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ታላቅ ታሪካዊ ገድል የፈጸመች ሲሆን፣ ይህም ግዙፍ ሀገራዊ አቅሟን በተግባር በማረጋገጥ ላይ ትገኛለች። ይህ ምድርን በአረንጓዴ ልምላሜ ያለበሰ ንቅናቄ የአፈር መሸርሸርን ከመግታት ባለፈ ለምግብ ዋስትና እና ለቀጣዩ ትውልድ የተተከለ የማይደርቅ የተስፋ ካስማ ሆኗል። ለዚህም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት መንግሥታት የግብርና እና ምግብ ድርጅት የተከበረውን የ"አግሪኮላ ሜዳልያ" ተሸላሚ ሆነዋል።

የዘመናት የቁጭታችን ማማ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በብዙ ውስብስብ ሴራዎች እና የመጓተት አረንቋ ውስጥ ወድቆ ከነበረበት ተነሥቶ፣ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቅቆ ወደ ፍጻሜው እንዲደርስ የተደረገው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ብረት የለበሰ ጽናት እና ቁርጠኝነት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቦታው በፀሐይ እና በቁር እየተመላለሱ፣ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን እና የጂኦ ፖለቲካ ሴራዎችን በዲፕሎማሲያዊ ብልሃት እየመከቱ፣ የኢትዮጵያውያን የልብ ትርታ የሆነው ግድብ በስኬት ተጠናቆ ለትውልድ እንዲበቃ አድርገዋል።

ከዚህም በዘለለ፣ ኢትዮጵያ በታሪክ ሂደት ካጣችው እና ከራቀችው የተፈጥሮ ሀብቷ ወደ ቀይ ባሕር እንድትመለስ የተከተሉት ግንባር ቀደም አመራር ታሪካዊ የታሪክ እጥፋት ነው። ለሦስት ዐሥርት ዓመታት የታፈነውን የባሕር በር እና የቀይ ባሕር ባለቤትነት ፍትሐዊ ጥያቄ ወደ አደባባይ በማውጣት፣ ኢትዮጵያ የመልክዓ ምድር እስረኛ ሆና እንዳትቀር፣ ፍላጎቷ በሰላማዊ መንገድ እና በጋራ ተጠቃሚነት መርህ እንዲከበር በማድረግ ረገድ ያሳዩት ቆራጥነት ሀገራችንን ወደ ተፈጥሯዊ የስትራቴጂ ማማዋ የመለሰ ድፍረት ነው።

የባሕር ኃይልን ዳግም በማቋቋም የቀይ ባሕር ቀጣናን ፍትሐዊ የትስስር መድረክ ለማድረግ የተያዘው ጽኑ አቋም፣ የኢትዮጵያን ዘመን ተሻጋሪ ጂኦ ስትራቴጂካዊ ተደማጭነት ዳግም አረጋግጧል።

የከተሞችን ገጽታ የቀየረው የኮሪደር ልማት፣ ዜጎች በሀገራቸው ታሪክ እና ውበት እንዲኮሩ ያደረጉት እንደ አንድነት፣ ወዳጅነት እና እንጦጦ ፓርኮች ያሉ የገበታ ለሸገር ድንቅ ሥራዎች፣ እንዲሁም በክልሎች የተንሰራፉት ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ሃላላ ኬላ እና ኮይሻ የተፈጥሮ ጸጋዎችን ወደ ኢኮኖሚ የለወጡ ሕያው ምስክሮች ናቸው።

በአዲሱ የገበታ ለትውልድ ማዕቀፍም በጨበራ ጩርጩራ እና በሌሎች የሀገራችን ክፍሎች የተገነቡት መዳረሻዎች ነባር አቅማችንን አውጥተው ተጨማሪ ገቢ እና የሥራ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ። በቢሾፍቱ የተጀመረው አዲሱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታም ሀገራችንን የአፍሪካ የአቪዬሽን ማዕከልነቷን ያጸናላታል።

ኢኮኖሚውን ከአንድ አቅጣጫ አውጥቶ በብዝኃ ዘርፍ እንዲያንሰራራ ለማድረግ በተተገበረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ የሀገራችን የገቢ አሰባሰብ እመርታዊ ለውጥ አስመዝግቧል።

የውጭ ዕዳ ጫናን በተሳካ ድርድር በማቃለልና የኢኮኖሚውን መዋቅር ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር የፋይናንስ መረጋጋት ተፈጥሯል። ጀማሪ ቢዝነሶችን፣ የአፍሪካ የመጀመሪያ የሆነውን የሰው ሠራሽ አስተውሎት (AI) ኢንስቲትዩት እና የዲጂታል ክፍያ ሥርዓቶችን በማስፋፋት ሀገራችንን ወደ ዘመናዊው ዓለም ያሸጋገረ የዝላይ መንገድ ተመንድጓል።

በዓለም አቀፍ መድረክ ድምጿ ጎልቶ የሚደመጥ፣ ክብሯ ወደ ላቀ ከፍታ የተሸጋገረ፣ ታላላቅ ኃያላን ሁሉ የሚፈልጓት እና ዓይናቸውን የሚጥሉባት፣ በቀጣናው አስተማማኝ ተጽዕኖ ፈጣሪ የሆነች ግዙፍ ኢትዮጵያ ዕውን ሆናለች።

ዲፕሎማሲያችን ከተከላካይነት ወደ አጀንዳ ሰጪነት ተቀይሮ የብሪክስ (BRICS) አባል መሆን ተችሏል። አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ጉባኤዎች ማዕከልነቷ ተጠናክሮ ኢትዮጵያ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ሁነቶችን የምታስተናግድ ተመራጭ መዳረሻ ሆናለች።

ኢትዮጵያ የጎረቤቶቿ አለኝታ፣ የአፍሪካ ድምፅ፣ የዓለም መሪዎች መድረሻ እና መናኸሪያ ሆናለች። ይህ ሁሉ ድል የተመዘገበው ተኝቶ በማደር ሳይሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዕረፍት አልባ የሌሊት እና የቀን ተጋድሎ፣ በመስዋዕትነት እና በተግባራዊ ገቢር ነበብ ሥራ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥልቅ ፍልስፍና የሀገራችንን ታሪካዊ ክብር ከዘመናዊ አሠራር ጋር በማዋሃድ በአጭር ጊዜ ውስጥ የማይታሰቡ ታላላቅ ድሎችን መሬት ላይ አስቀምጧል።

ዛሬ ላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህንን የተግባር አመራር፣ ይህንን የማይደክም ብርቱ ክንድ፣ ይህንን የትንሣኤ ፋና አይቶ ዳግም ድምፁን ሰጥቷል። የመደመር መንግሥት በሕዝብ ይሁንታ ዳግም መመረጡ፣ የተጀመሩትን የልማት ምዕራፎች የማጽናት እና ኢትዮጵያን አፍሪካዊ የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይን የማስፈጸሚያ ታላቅ ጉልበት ነው።

ይህ የሕዝብ ድምፅ ከአምስት ዓመታት የፈተና እና የድል ጉዞ በኋላ፣ መንግሥት በሠራቸው የማይፋቁ አሻራዎች የታመነበት እና ወደፊትም ከዚህ የገዘፉ ታላላቅ ሀገራዊ ራዕዮችን እንዲያሳካ የተሰጠ አዲስ የታሪክ አደራ ነው።

የመደመር መንግሥት ዛሬም በተግባር አመራሩ፣ በፈተና የማይበገረው ጽናቱ እና ፍልስፍናው ይበልጥ ጸንቶ እየገሰገሰ ነው። ይህ ድምፅ የትላንት ድሎችን የማስቀጠል፣ የዛሬን ስኬቶች የማላቅ እና የነገዋን ታላቅ ኢትዮጵያ ያለ ጥርጥር ዕውን የማድረግ የጽናት ውል ነው። የመደመር መንግሥት አሁንም በሥራው፣ በአሻራው፣ በክብሩ እና በልዕልናው ዳግም ወደፊት እየመጣ ነው!

በአዶኒያስ ወልደአረጋይ

#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: