ዛሬ አዲሱ የመደመር መንግሥት ሲመሠረት ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ከፖለቲካዊ ስብራት እና ከኢኮኖሚያዊ ድቀት በመውጣት በመደመር እሳቤ ላይ የገነባችውን አዲስ ሀገራዊ መሠረት በመያዝ ወደ ላቀ ምዕራፍ የምትሸጋገርበት ታሪካዊ ዕለት ነው።
ይህ የሪፎርም ጉዞ ከተለመደው የዕርዳታ ጥገኝነት በመውጣት፤ መንግሥት፣ ገበያና ማኅበረሰብ በተቀናጀ ኃላፊነት ሀገር ግንባታን እንዲመሩ ያስቻለ የታሪክ እጥፋት ነው።
ምንም እንኳን ዓለም አቀፍና የሀገር ውስጥ የኢኮኖሚ ጫናዎች፣ የዋጋ ንረት፣ የጸጥታ ስጋቶችና የአየር ንብረት መዛባቶች እጅግ ፈታኝ ቢሆኑም፣ ኢትዮጵያ እነዚህን ተግዳሮቶች በጽናት ተቋቁማ በሁሉም ዘርፎች መዋቅራዊ ሽግግሮችን አስመዝግባለች።
ከእነዚህም ድሎች መካከል ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ግንባር ቀደም ነው። የውጭ ምንዛሪ አስተዳደርን በገበያ መር ሥርዓት በመተካት ማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት እንዲሁም ብሔራዊ ባንክ ለመንግሥት የሚሰጠውን ቀጥተኛ ብድር ማቆም ተችሏል።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከግዙፍ ዕዳ በማላቀቅ፣ የካፒታል ገበያን በመመሥረትና የባንክ ዘርፉን ክፍት በማድረግ ከፍተኛ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ ተችሏል።
በዚህም ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርት ከ205 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሲደርስ፣ የነፍስ ወከፍ ገቢም ከእጥፍ በላይ በማደግ 1 ሺህ 600 ዶላር ደርሷል።
ይህ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት በግብርናውና በኢንዱስትሪው ዘርፍ በተገኙ ተጨባጭ ስኬቶች የታጀበ ነው።
ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በተከናወነው የበጋ መስኖ የስንዴ ልማት፣ ኢትዮጵያ ከራስ ፍጆታ አልፋ ምርቷን ለውጭ ገበያ ማቅረብ ችላለች።
በሶማሌ ክልል ጎዴ በመገንባት ላይ ያለው ግዙፉ የማዳበሪያ ፋብሪካም የምግብ ሉዓላዊነትን በዘላቂነት የሚያረጋግጥ ነው።
በተጓዳኝም "ኢትዮጵያ ታምርት" በሚለው ንቅናቄ በመቶዎች የሚቆጠሩ አምራች ኢንዱስትሪዎች ወደ ሥራ በመመለሳቸው የማምረት አቅም ከ67 በመቶ በላይ ደርሷል።
96 ዓይነት ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ማዳን የተቻለ ሲሆን፣ የሀገር ውስጥ ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች ያላቸው ተሳትፎም በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።
በሌላ በኩል ቴክኖሎጂን የልማት ምሰሶ ያደረገው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ፣ ኢትዮጵያን ከአገልግሎት ተጠቃሚነት ወደ አመንጪነት እያሸጋገራት ይገኛል።
ከ50 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ያቀፈው የ"ፋይዳ" ብሔራዊ ዲጂታል መታወቂያ፣ የ"5 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ኮደሮች" ኢኒሼቲቭ እንዲሁም 16 ትሪሊዮን ብር ያንቀሳቀሰው የዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓት፣ ዘመናዊና አካታች ኢኮኖሚን እውን እያደረጉ ነው።
በተጨማሪም በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የተከናወኑት የወንዞች ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ሥር ነቀል የከተማ ትራንስፎርሜሽን አምጥተዋል።
እነዚህ ልማቶች ከተሞችን አረንጓዴ ከማድረግ እና የጎርፍ አደጋን ከመከላከል ባለፈ፣ ሰፊ የሥራ ዕድል የፈጠሩና የሀገር ውስጥ ባለሙያዎችን አቅም በተግባር ያሳደጉ ናቸው።
ባለፉት አምስት ዓመታት የተሠሩት ግዙፍ የመሠረተ ልማት ሥራዎች፣ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የታዳሽ ኃይል እመርታ፣ የተካሄደው ሀገራዊ ምክክር እንዲሁም የተሳካው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር ተዳምረው የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ ያበሰሩ ናቸው።
ዛሬ የሚመሠረተው አዲሱ የመደመር መንግሥት፣ እነዚህን በፈተና ውስጥ ያለፉ ጽኑ መሠረቶች በመጠቀም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና እውን የማድረግ ታሪካዊ አደራ ተጥሎበታል።
በቀጣዮቹ ዓመታት ከአዲሱ መንግሥት በዋናነት ከሚጠበቁ ተግባራት መካከል፣ የተጀመረውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፍሬ ወደ ታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል በማውረድ የዋጋ ንረትን መቆጣጠርና የዜጎችን የኑሮ ጫና በዘላቂነት ማቃለል ዋነኛው ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የተጀመረውን ሀገራዊ ምክክር ወደ ላቀ ብሔራዊ መግባባት በመቀየር ዘላቂ ሰላምን በጽኑ መሠረት ላይ ማቆምና የዜጎችን ደኅንነት የሚያረጋግጥ የሕግ የበላይነትን ማስፈን የቅድሚያ ትኩረቶች ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በቀጣዩ ጉዞ የኢትዮጵያን ዕድገት በኢኮኖሚው ዘርፍ ብቻ ሳይወሰን፣ በጥቅሉ ሰፋ ወዳለ ሀገራዊ ትራንስፎርሜሽን ማሳደግ ግድ ይላል።
የዲጂታል ትራንስፎርሜሽኑን፣ የአምራች ኢንዱስትሪውን እና የግብርናውን ዘርፍ ከዓለም አቀፍ የንግድ ሥርዓት ጋር በማስተሳሰር እንዲሁም የቀይ ባሕር ቀጣናዊ ትስስርንና የወደብ ዲፕሎማሲን ማዕከል ያደረገ ስትራቴጂካዊ የውጭ ግንኙነትን በማጠናከር ብሔራዊ ጥቅምን በተግባር ማረጋገጥ፣ ከአዲሱ መንግሥት የሚጠበቁ ቁልፍ የትኩረት አቅጣጫዎች ናቸው።
ዛሬ የሚመሠረተው አዲሱ የመደመር መንግሥት፣ ኢትዮጵያ በችግሮቿ ሳይሆን በእምቅ አቅሟ፣ በተግባራዊ ስኬቷና ቀጣይነት ባለው መዋቅራዊ ዕድገቷ የምትገለጽበት አዲስ ምዕራፍ ላይ የቆመች ሀገር መሪ በመሆን፤ የተጀመሩ ራእዮችን በማሳካት ለቀጣዩ ትውልድ የሚሻገርና የማይናወጥ የጽናት መሠረት የመገንባት ኃላፊነት ተሸክሟል።
በበረከት ሽመልስ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: