Search

“ተንገዳገድን እንጂ አልወደቅንም፤ ከእንግዲህም አንወድቅም!” — ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ሰኞ መስከረም 25, 2019 84

ኢትዮጵያ በትውልድ ቅብብሎሽ ያበበውን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ውርስ በመመርመር፣ ከባሕር ማዶ የሚገኙ ጠቃሚ ዕውቀቶችን ከኢትዮጵያዊ እሳቤ ጋር በማጣጣምና የጎደለውን በመሙላት ጠንካራ ሥልጣኔ መገንባት መቻሏን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም የሌሎች እሳቤ ኢትዮጵያን እንዲቀይር ከመፍቀድ ይልቅ ለሀገር ጥቅም ሲባል የሌሎችን እሳቤ አቃንቶ መቀበል ተገቢ አካሄድ መሆኑን ጠቁመዋል።

ባለፉት ዓመታት የተደረገው የ“መደመር” ጥረትም የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ማሰቢያ ቋንቋ መሆን እንደሚችል በተጨባጭ ማረጋገጡን አስታውቀዋል።

ዛሬ ላይ በከተሞች እና በገጠራማ አካባቢዎች እኩል ለውጥ እየመጣ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፣ የኮሪደር ልማት የከተሞችን የቀድሞ ገመና ገላልጦ ማሳየቱን ገልጸዋል።

በስመ ከተማ ተጠርተው ኢትዮጵያን ሞልተዋት የነበሩ ለኑሮ፣ ለመናኸሪያ እና ለስብሰባ ያልተመቹ፣ ሕይወት በሰቆቃ የሚገፋባቸው እና ንግድ እንዲሁም አገልግሎት የማይሳለጥባቸው መንደሮች ዛሬ መልካቸውን በመቀየር ለኑሮ የተመቹ፣ ለንግድ እና ለኮንፈረንስ የተስማሙ እንዲሁም ተምሳሌት ሆነው የሚጠቀሱ ዘመናዊ ከተሞች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ይህም ኢትዮጵያን ባዶ ውዳሴ ባልሆነ መልኩ እውነተኛዋ “የአፍሪካ ውብ አበባ” እንድትባል ማስቻሉን ተናግረዋል።

በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር 56 ቢሊዮን ችግኞች በመተከላቸው የተራቆቱ ሜዳዎች ለምለም አረንጓዴ መጎናጸፋቸውንና የአፈር መሸርሸር መገደቡን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የበጋ መስኖ ልማት የስንዴና የሩዝ ታሪክን መለወጡን እንዲሁም የሌማት ትሩፋት የወተት፣ የዶሮና የእንቁላል ምርቶችን በማሳደግ በምግብ ራስን የመቻል ግብ ሩቅ እንዳልሆነ ማሳየቱን አብራርተዋል።

ከዚህም ጎን ለጎን የመሶብ የሕዝብ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የፋይዳ ዲጂታል ብሔራዊ መታወቂያ ሥርዓት፣ የወንዝ ዳር ልማት፣ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች፣ የአዲስ አበባ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም መስህብነት፣ የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የምርት ባህል ዕድገትና የማዕድን ልማት የወጪ ንግድን በአጭር ጊዜ ውስጥ በማሳደግ ረገድ ተጨባጭ የማድረግ አቅም ማሳየታቸውን አንስተዋል።

ኢትዮጵያ ፎክረው እንደሚገዙ ሳይሆን ተጋድለው ነፃነታቸውን እንደሚያስከብሩ ድንቅ ጀግኖች ሀገር፣ ዳግም ፍላጎቶቿን በራሷ መንገድ እንደምታረጋግጥ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ያለፉት ዓመታት ሰንኮፉን ለመንቀል፣ አረሙን ለማረም፣ እንቅፋቱን ለመንሳት፣ መንገዱን ለመጥረግና መሠረቱን ለመጣል የታገልንባቸው እንደነበሩ አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው “መንገዳችን ቀና፣ ዓላማችን ሁነኛ፣ መዳረሻችን አመርቂ፣ አካሄዳችን ትክክል መሆኑን ሠርተን አረጋግጠናል፤ በእንቅፋቶች ሳይወድቅ ተገቢውን ምላሽ እየሰጠ የሚሄድ የማይበገር የፖለቲካል ኢኮኖሚ ሥርዓት እየገነባን ነው” ብለዋል።

አያይዘውም “በወንዛችን የመጠቀም መብታችንን ለማስከበር ደፋ ቀና ስንል፣ ግድባችንን ከፍጻሜ እንዳናደርስ በረጅም ገመድ አስረው ሲጎትቱን ተንገዳገድን እንጂ አልወደቅንም፤ ከእንግዲህም አንወድቅም” ሲሉ የኢትዮጵያ የማይበገር የከፍታ ጉዞና የማድረግ አቅም አረጋግጠዋል።

በጌቱ ላቀው

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: