የባሕር በር ተጋሪነታችን የተለወጠው፣ የተጽዕኖ አድማሳችን ሲኮሰምን የኖረው ፈልገን ብቻ አይደለም፤ ተገድደን ጭምር ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በ7ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የምክር ቤቱ መመስረቻ 1ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ንግግር አድርገዋል።
በንግግራቸውም ዛሬም ያለንበት ጂኦ-ፖለቲካዊ ሁኔታ በፍጥነት እየተለዋወጠ እንደሚገኝ አንስተው፤ በዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ጠንክረን መጋፈጥ ከቻልን እንደምናሸንፍ እሙን ነው፤ ደክመን ከተገኘን ግን ሽንፈት የምንጎነጨው ጽዋ መሆኑ አይቀሬ ነው ብለዋል።
አቅም በነበረን ወቅት የራሳችን ጉዳይ እራሳችን ወስነናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በተዳከምን ጊዜ ግን ሌሎች በእኛ ላይ ወስነውብናል ሲሉ ገልጸዋል።
በዚህ ጊዜ ቶሎ የነቁ እና ድርጅታዊ አቅም የገነቡ አካላት ማሸነፋቸው አይቀሬ መሆኑን ጠቁመው፤ እኛም ይህንን አዲስ ምክር ቤት የምንጀምረው ቀጣናችን በዚህ የለውጥ ነፋስ እየተመታ ባለበት ወቅት እንደሆነ አጽንዖት ሰጥተዋል።
በማዕበል በምትናወጥ ዓለም ውስጥ እስከምን ለመጓዝ ተዘጋጅተናል ለሚለው ጥያቄ ምላሹ ከእያንዳንዳችን የሚጠበቅ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) አስገንዝበዋል።
#ትልቅ_ሀገር! #ትልቅ_ሕዝብ! #ታላቅ_ርዕይ!
በአድማሱ አራጋው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: